ሳዑዲ ከኳታር ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር ለመክፈት ተስማማች
ይህን ተከትሎ የኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ ዛሬ በሪያድ በሚጀመረው የባህረሰላጤው ሃገራት ጉባዔ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል
ሃገራቱ የአየር እና የየብስ ግንኙነት ማድረግ መጀመራቸውም ተነግሯል
ከኳታር ጋር ለ3 ዓመታት በዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔ ውስጥ የነበረችው ሳዑዲ አረቢያ ከዶሃጋር የምትዋሰንበትን ድንበር ለመክፈት ተስማማች፡፡
ሪያድ ከዶሃ ጋር የአየር እና የየብስ ግንኙነት ለማድረግ ከሚያስችላት ስምምነትም ደርሳለች፡፡
ሃገራቱ ቅራኔያቸውን ፈተው ወደ ቀደመ ግንኙነታቸው እና ትብብር እንዲመጡ ስታሸማግል የነበረችው ኩዌት ከትናንት ሰኞ ምሽት ጀምሮ የድንበር በሮቹ ክፍት እንደሚሆኑ አስታውቃለች፡፡
ኳታርም በበኩሏ በዓለም የንግድ ድርጅት እና በዓለም አቪዬሽን ባለስልጣን ጀምራው የነበረውን የክስ ሂደት ታቋርጣለች እንደ ፋይናንሺያል ታይምስ ዘገባ፡፡
ስምምነቱን ተከትሎ የኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ታኒ ዛሬ በሪያድ በሚጀመረው የባህረሰላጤው ሃገራት ጉባዔ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡
ይህ የሚሆን ከሆነ ከባለፉት 3 ዓመታት ወዲህ የአል-ታኒ የመጀመሪያው የሳዑዲ ጉዞ ነው የሚሆነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 ግብጽን ጨምሮ ሳዑዲ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች (ዩ.ኤ.ኢ) እና ባህሬይን ሽብርተኝነትን ትደግፋለች በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ትብብር ማቋረጣቸው የሚታወስ ነው፡፡
ዛሬ የሚጀመረው ጉባዔ ስምምነቱን የተከተሉ ውይይቶች የሚደረጉበት እና ዝርዝር መረጃዎች ይፋ የሚደረጉበት ሊሆን እንደሚችልም ተነግሯል፡፡
ጉባዔው ከአሁን ቀደም በዲፕሎማሲያዊ ቅራኔ ውስጥ የነበሩትን የቀጣናውን ሃገራት በማቀራረብ ወደ አንድነት እና ወደ ትብብር የሚያመጣ እንደሚሆን አስታውቃለች፡፡
የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ መሃመድ ቢን ሳልማን ቅራኔው እንዲፈታ ፍላጎት ከማሳደር ጀምሮ የጎላ ሚና እንዳላቸው ይነገራል፡፡
ቀጣናው ከተጋረጡበት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ፊት ሃገራቱ እንዲተባበሩ ያስችላል በሚል ስለ ጉባዔው እና ስለ ስምምነቱ ስለመናገራቸውም የሳዑዲ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ልዑል አልጋወራሹ የትራምፕ አስተዳደር ከመሰናበቱ በፊት ይህ ጉዳይ መቋጫ እንዲያገኝ እና ከአዲሱ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው እንደሚሹ ተነግሯል፡፡
ለስምምነቱ ዳር መድረስ የትራምፕ አስተዳደር ትልቅ ሚና ሲጫወት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላምም እንዲሁ ሲሰራ እንደነበር መነገሩም አይነጋም፡፡
ሳዑዲ ዛሬ 41ኛውን የባህረ ሰላጤው ሃገራት የትብብር ጉባዔን ታስተናግዳለች፡፡ በጉባዔው ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የኳታሩን ኢምር ጨምሮ ሌሎች የቀጣናው ሃገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡
የኤመራቱ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል-መክቱም በጉባዔው ለመሳተፍ ወደ ሪያድ ስለማቅናታቸውም ዋም የተሰኘው የሃገሪቱ የዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡