“የዩኤኢ እና የኳታር ህዝብ በደም የተሳሰረ እና ወንድማማች ነው” - ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም
“የባህረ ሰላጤው ሃገራት መጻዒ እድል አንድ መሆን ነበር፤ አሁንም ነው” ሲሉም ነው የዩኤኢ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢው ያሳሰቡት
የዩኤኢ ምክትል ፕሬዝዳንት በባግዳድ ከኳታር ኢምር ጋር ተወያይተዋል
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ አል መክቱም “የዩኤኢ እና የኳታር ህዝብ በደም የተሳሰረ እና ወንድማማች ነው” ሲሉ ተናገሩ፡፡
የዩኤኢ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢ የሆኑት አል መክቱ ዛሬ በሚጀመረው ቀጣናዊ የትብብር ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኢራቅ ባግዳድ አቅንተዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንቱ በባግዳድ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከኳታር ኢምር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ጋር መገናኘታቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡
በማህበራዊ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ሃገራቸው ከኳታር ህዝብ ጋር “በደም የተሳሰረ እና ወንድማማች” ግንኙነት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
“የባህረ ሰላጤው ሃገራት መጻዒ እድል አንድ መሆን ነበር፤ አሁንም ነው” ሲሉም ነው የዩኤኢ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዱባይ ገዢው አል መክቱም ያሳሰቡት፡፡
“ልዑል ታሚም ወንድምና ጓደኛ፤ የኳታር ህዝብም ወገን ወንድምም ነው የሰላጤው እጣ ፋንታ አንድ ነበር ነውም” የሚል ጽሁፍንም አስፍረዋል፡፡
ሼክ መሃመድ ቢን ረሺድ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ነው ቀድመው ወደ ኢራቅ ያቀኑት፡፡ ባግዳድ በደረሱ ጊዜም በጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አል ካዜሚ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ዩኤኢ እና ኳታር ከ2017 ወዲህ ተቋርጦ የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማለሳለስና ዳግም ለማስቀጠል በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት መባቻ ግድም ተስማምተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በጉባዔው የፈረንሳዩን ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮንን ጨምሮ የሳዑዲ፣ የዮርዳኖስ፣ የግብጽ እና የሌሎችም የቀጣናው ሃገራት እና ተቋማት መሪዎች ይሳተፋሉ፡፡