የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የኳታር ልዑካን በኩዌት እየተወያዩ ነው
ኳታር እና ዩኤኢ ለዓመታት የነበራቸውን ቅራኔ ከአል-ኡላ ጉባዔ በኋላ ለመፍታት መወሰናቸው ይታወሳል
ሁለቱ ወገኖች የአል-ኡላ ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ የጋራ ተግባራት ላይ ተወያይተዋል
በቅርቡ በሳዑዲ ከተማ አል-ኡላ በተካሄደው የባህረ ሰላጤው ጉባዔ የተላለፈውን ‘የአል-ኡላ መግለጫ’ ተከትሎ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረገው የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን እና ኳታርን የሚወክሉ ሁለት ይፋዊ ልዑካን ዛሬ ሰኞ በኩዌት ተገናኝተዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች የአል-ኡላ ውሳኔን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ የጋራ ተግባራት ላይ ተወያይተዋል፡፡ የባህረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት መንግስታት እና ዜጎቻቸውን ፍላጎት ለማርካት ፣ የባህረ ሰላጤውን ትብብር መጠበቅ እና የጋራ ተግባራትን ማጠናከር እንዲሁም በቀጣናው መረጋጋት እና ብልጽግና የማስፈን አስፈላጊነት ላይ መምከራቸውም ነው የተገጸው፡፡
ሁለቱም ወገኖች ፣ ኩዌት የሁለቱን ሀገራት የመጀመሪያ ስብሰባ ከማስተናገድ በተጨማሪ ፣ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት እና የባህረ ሰላጤውን ጉዞ ለመደገፍ ላደረገችው ጥረት ፣ ለሀገሪቱ አሚር ሼክ ናዋፍ አሕመድ አል-ጀበር አል ሳባህ ምስጋናቸውን እና አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ጥር ወር በሳዑዲ አረቢያ አስተናጋጅነት በአል-ኡላ የተካሄደው 41ኛው የባህረ ሰላጤው ጉባዔ ፣ በባህረ-ሰላጤው ሀገሮች መካከል የፀጥታ እና ወታደራዊ ትብብርን ለማጎልበት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ከኳታር ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ ሀገራትም መግባባት ለመፍጠር የተስማሙ ሲሆን ይህን ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የባህር ፣ የየብስ እና የአየር ድንበራቸውን ለኳታር ክፍት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡