ግብጽ ከእስራኤል ጋር ያደረገችውን 40 አመታት ያስቆጠረ ስምምነት ውድቅ እንደምታደርግ አስፈራራች
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሰላም፣ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል በተደረጉ ተከታታይ ጦርነቶች እክል አልገጠመውም ነበር
የግብጹ ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜንቸም ቤጊን የፈረሙት ስምምነት ላለፉት 40 አመታት በእስራኤል እና ግብጽ መካከል ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል
ግብጽ ከእስራኤል ጋር ያደረገችውን 40 አመታት ያስቆጠረ ስምምነት ውድቅ አደርጋለሁ ስትል አስፈራራች።
የግብጹ ፕሬዝደንት አንዋር ሳዳት እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜንቸም ቤጊን በካምፕ ዴቪድ ሜሪላንድ የፈረሙት ስምምነት ላለፉት 40 አመታት በእስራኤል እና ግብጽ መካከል ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል።
ስምምነቱ በቀጣናው ወሳኝ የሰላም ምንጭ ህኖ እያገለገለ ይገኛል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ሰላም፣ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል በተደረጉ ተከታታይ ጦርነቶች እክል አልገጠመውም ነበር።
ነገርግን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በግብጽ ድንበር ወደምትገኘው የጋዛዋ ራፋ ከተማ ጦር እንደሚያዘምቱ መግለጻቸውን ተከትሎ የግብጽ መንግስት ስምምነቱን እንደሚሽረው እያሰፉራራ ነው።
የስምምነቱ ታሪክ ምን እንደሚመስል እና ስምምነቱ ቢጣስ ምን ሊከሰት እንደሚችል ኤፒ እንደሚከተለው ዘርዝሮታል።
ስምምነት መነሻ ምንድነው?
በፈረንጆቹ 1977 የያኔው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤጊን እስራኤል ከአስርት አመታት በፊት ቀደም ብላ የ1967ቱን ጦርነት አሸንፋ የያዘችውን የትኛውንም መሬት አልሰጥም በሚል ተቃወሙ። እስራኤል ከያዘቻቸው መሬቶች ውስጥ የግብጽም አካል የሆነው የሲናይ ግዛት ይገኝበት ነበር።
እስራኤል እና ግብጽ በ1973 አራት ትላልቅ ጦርነቶችን አካሂደዋል። የግብጽ መሪ አንዋር ሳዳት ከሌሎች የአረብ መሪዎች በመነጠል ከእስራኤል ጋር ለመነጋገር ሲወስን አለምን አስገርሞ ነበር።
ንግግሩ በ1978 በካሞፕ ዴቪድ አብቅቶ፣ የሰላም ስምምነቱ ከአንድ አመት በኋላ ተፈርሟል።
በስምምነቱ መሰረት እስራኤል ይዛው ከነበረው ሲናይ ግዛት ጦሯን ያስወጣች ሲሆን ግብጽ የእስራኤል መርከቦች ቁልፍ በሆነው የንግድ መስመር ሱይዝ ቦይ እንዲያልፉ ፍቃድ ሰጠች።
እስራኤልም በአረብ ሀገር የመጀመሪያዋን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከግብጽ ጋር መጀመር ቻለች።
የግብጽ ወቅታዊ አቋም
የእስራኤል ጦር ራፋን የሚወር ከሆነ ግብጽ ስምምነቱን ልታቋርጥ እንደምትችል ኤፒ ሁለት የግብጽ ባለስልጣናትን እና ምዕራባዊ ዲፕሎማትን ጠቅሶ ዘግቧል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የሀማስ የመጨረሻዎቹ አራት ምሽጎች በራፋ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ነገርግን ግብጽ ፍልስጤማውያንን ወደ ግብጽ ሊያሳድድ የሚችል ማንኛውንም አይነት እርምጃ ትቃወማለች።
ዙሪያዋን በተከበበችው ጋዛ ውስጥ ብቸኛ የሰብአዊ እርዳታ ማስተላለፊያ የሆነችው ራፋ ጦርነት ሸሽተው የመጡትን ጨሞሮ 1.4 ሚሊዮን ሰዎችን እያስተናገደች ነው።
ኔታንያሁ በራፋ ጥቃት ከመጀመሩ በፊት ጦሩ ንጹሃን ከአካባቢው የሚወጡበትን እቅድ እንዲያወጣ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
ግብጽ በድንበር አካባቢ ጦርነቱ ሲደረግ መሄጇ የሚያጡ ፍልስጤማውያን ወደ ግዛቷ ሊገቡ ይችላሉ በሚል ነው የእስራኤልን የራፋ የጥቃት እቅድ የተቃወመችው።
ስምምነቱ ቢጣስ ምን ይከሰታል?
ስምምነቱ በሁለቱም በድንበር በኩል ያሉ የወታደሮችን ቁጥር በእጅጉ ይገድባል። ይህ እስራኤል ወደ ሌላ ቦታ ትኩረት እንድታደርግ አስችሏታል።
እስራእል በጋዛ ከምታደርገው ጦርነት በተጨማሪ በሰሜን በኩል ከሊባኖሱ ሄዝቦላ ጋር ተኩስ እየተለዋወጠች ነው። በዌስትባንክም ብዛት ያለው ወታደር አሰማርታለች።
ግብጽ ስምምነቱን የምታቋርጠው ወይም የምትጥሰው ከሆነ እስራኤል በደቡብ ያለውን ድንበሯን የሰላም ቀጣና አድርጋ ማየቷ ያበቃል ማለት ነው።
በግብጽ ድንበር በኩል የወታደር ስምሪት ማድረግ የተበታተነውን የእስራኤል ጦር ይፈትነዋል። ነገርገን ከስምምነቱ ወዲህ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ወታደራዊ እርዳታ ከአሜሪካ ለምታገኘው ግብጽም ስምምነቱን መጣስ ቀላል አይሆንላትም።