ሳኡዲ አረቢያ ነጻ የፍልስጤም ሀገር ሳይመሰረት ከእስራኤል ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደማታደርግ ገለጸች
ሳኡዲ አረቢያ በ1967 ስምምነት መሰረት ነጻ የፍልስጤም ሀገር ካልተመሰረት ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደማይኖራት ለአሜሪካ ተናግራለች
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሳኡዲ አረቢያ በአሜሪካ የሚደገፈውን ግንኙነት የማደስ ሂደት ውሃ ቸልሳበታለች ተብሏል
ሳኡዲ አረቢያ ነጻ የፍልስጤም ሀገር ሳይመሰረት ከእስራኤል ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንደማታደርግ ገለጸች።
ሳኡዲ አረቢያ በ1967 ስምምነት መሰረት ነጻ የፍልስጤም ሀገር ካልተመሰረት እና እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወረራ ካላቆመች ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደማይኖራት ለአሜሪካ ተናግራለች።
በትናንትናው እለት የኃይትሀውስ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ክርቢይ የባይደን አስተዳደር ሳኡዲ አረቢያ እና እስራኤል ግንኙነት የማደስ ንግግር ለመጀመር ፈቃደኛ ናቸው ብለው ነበር።
ነገርግን ሳኡዲ አረቢያ በፍልስጤም ጉዳይ ያላትን ጥብቅ አቋም የሚያሳይ መግለጫ አውጥታለች።
ሁለቱ የገልፍ ጎረቤቶቿ አረብ ኢምሬትስ እና ባህሬን በፈረንጆቹ በ2020 ግንኙነት ከጀመሩ በኋላ የሳኡዲ እና የእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመር ጉዳይ ንግግር ሲደረግበት ቆይቷል።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሳኡዲ አረቢያ በአሜሪካ የሚደገፈውን ግንኙነት የማደስ ሂደት ውሃ ቸልሳበታለች ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሁለት ቀናት በፊት ለአምስተኛ ጊዜ ባደረጉት የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸው ሳኡዲ አረቢያን ጎብኝተው ተመልሰዋል።
ብሊንከን አሜሪካ የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ቆሞ፣ የእስራኤል-ሳኡዲ አረቢያ ግንኙነት የማደስ እና የፍልስጤም ሀገር ምስረታ ሂደቶች እንዲፋጠኑ እንደምትፈልግ ተናግረዋል።