የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃሚየህ ዛሬ ግብጽ ይገባሉ
በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት በቀረበው የተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያም የሃማስን አቋም ያሳውቃሉ ተብሏል
እስራኤል ግን ጦሯን ከጋዛ እንድታስወጣ የሚጠይቅ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማትቀበል አስታውቃለች
የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃሚየህ ለመድረስ ዛሬ ግብጽ ይገባሉ።
ሃማስ በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት የቀረበውን የስድስት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት እያጤነው መሆኑን ቀደም ብሎ ማስታወቁ ይታወሳል።
በፓሪስ በተካሄደውና የአሜሪካው የማዕከላዊ ምርመራ ቢሮ (ሲአይኤ) ሃላፊ ዊሊያም በርንስ የተሳተፉበት የተኩስ አቁም ረቂቅ ሰነድ በሶስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው ተብሏል።
ጦርነቱ ለስድስት ሳምንት እንዲቆም ተደርጎ ሃማስ ሴቶች፣ ህጻናትና የታመሙ ታጋቾችን እንዲለቅ እስራኤልም የፍልስጤም እስረኞችን እንድትፈታ የሚጠይቀው ረቂቅ ሰነድ በሃማስ በኩል ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚችል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር ከጋዛ ስለሚወጣበት ሁኔታም በእነዚህ ስድስት ሳምንታት ድርድር ይደረጋል ይላል ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ሰነዱ።
ሃማስን ካልደመሰስኩ ከጋዛ አልወጣም ያለችው እስራኤል ግን መሰል የድርድር ሃሳብ ያለበትን ስምምነት አልፈርምም ማለቷን ሬውተርስ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሺዎች የሚቆጠሩ የፍልስጤም እስረኞችን መልቀቅም ሆነ ከጋዛ መውጣትን የሚጠይቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አንደርስም ብለዋል።
በታህሳስ ወር ግብጽ የገቡት ኢስማኤል ሃኒየህ ዛሬ ዳግም ወደ ካይሮ ማምራታቸው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚደረስ ተስፋ ቢደረግም የቴል አቪቭ አቋም የሚለወጥ አይመስልም።
የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት በኳታርና ግብጽ ሸምጋይነት የሚደረገውን ድርድር “ገንቢ ነው” ከማለት ውጭ ዝርዝር ጉዳዮችን አልጠቀሰም።
እስራኤላውያን የታጋቾች ቤተሰቦች ግን አሁንም ድረስ በጋዛ የሚገኙ 132 ወገኖቻቸው እንዲለቀቁ የኔታንያሁ መንግስት ስምምነት ላይ እንዲደርስ መጠየቃቸውንና ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል።