ግብጽ፤ እስራኤል በራፋ የእግረኛ ጦር ጥቃት እንዳትጀምር አስጠነቀቀች
ኳታር እና ሳኡዲ አረቢያም በተመሳሳይ አደጋው የከፋ ይሆናል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል
ኔታንያሁ በራፋ ያሉትን አራት ምሽጎች ትቶ ሀማስን ማጥፋት የማይታሰብ ነው ብለዋል
ግብጽ፤ እስራኤል በራፋ የእግረኛ ጦር ጥቃት እንዳትጀምር አስጠነቀቀች።
የእስራኤል ጎረቤቶች እና ቀልፍ የሚባሉት አደራዳሪዎች እስራኤል በጋዛዋ ደቡባዊ ከተማ ራፋ በእግረኛ ጦር ማጥቃት የምትጀምር ከሆነ አስከፊ የሆነ ውጤት ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
እስራኤል የሀማስ የቀረው ምሽጉ በራፋ እንደሚገኝ መግለጿ ይታወሳል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በራፋ ወረራ ከመጀመሩ በፊት ጦሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለቀው የሚወጡበትን እቅድ እንዲያወጣ መጠየቃቸውን ከተናገሩ ከሰአታት በኋላ 44 ፍልስጤማውያን በአየር ጥቃት ተገድለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከፍተኛ መረበሽን ፈጥሯል። ከ2.3 ሚሊዮን የጋዛ ህዝብ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚኖረው በግብጽ ድንበር በምትገኘው የራፋ ከተማ ነው።
አብዛኛው ህዝብ ወደ ራፋ የተሰደደው በሀማስ ላይ ጥቃት የከፈተችው እስራኤል ነዋሪዎች ቦታ እንዲለቁ ያስተላለፈችውን ማስጠንቀቂያ ተከትሎ ነው።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሾከሪ እስራኤል በራፋ የምታደርገው ጥቃት "አስከፊ ውጤት" ይኖረዋል፣ ይህም የእስራኤልን ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው የማስወጣት እቅድ ያረጋግጣል ብለዋል።
ግብጽ ምንም አይነት ወደ ግብጽ ምድር የሚደረግ የፍልስጤማውያን እንቅስቃሴ በእስራኤል እና በግብጽ መካከል የተፈረሙን የ40 አመቱን የሰላም ስምምነት አደጋው ውስጥ ይከተዋል ስትል አስጠንቅቃለች።
ኳታር እና ሳኡዲ አረቢያም በተመሳሳይ አደጋው የከፋ ይሆናል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል በራፋ አደርገዋለሁ ባለች የእግረኛ ጦር ጥቃት ጉዳይ ሰላማዊ ዜጎችን በማስወጣት እቅዷ ዙሪያ ከአጋሯ አሜሪካም ጋር አልተስማማችም።
ኔታንያሁ በራፋ ያሉትን አራት ምሽጎች ትቶ ሀማስን ማጥፋት የማይታሰብ ነው ብለዋል። ኔታንያሁ ከፍተኛ ትችት ቢሰነዘርባቸውም፣ ወደኋላ እንደማይሉ ተናግረዋል።