ፕሬዝዳንት አልሲሲ ሶማሊያ አረብ መሆኗን እና አረቦች በጋራ ሊጠብቋት ይችላሉም ብለዋል
ግብጽ ከሶማሊያ ጥያቄ ከቀረበላት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎ ሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትላት ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ግብጽ ለሶማሊያ ሉዓላዊነት ድጋፍ አደርጋለሁ ያለች ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነትንም እንደማትደግፍ አስታውቃለች፡፡
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ግብጽ ማምራታቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን ከውይይቱ በኋላም የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት አልሲሲ እንዳሉት "ለኢትዮጵያ ያለኝ መልዕክት አንድን መሬት ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት አይሳካም በዚህ የሚስማማም የለም" ብለዋል፡፡
“ሶማሊያ አረብ ሀገር ናት፣ በአረብ ሊግ ቻርተር መሰረትም አረቦች ከጥቃት እንዲጠብቋት የመጠየቅ እና የመጠበቅ መብትም አላት“ ሲሉም ፕሬዝዳንት አልሲሲ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም "የሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት ተቀባይነት የሌለው ነው፣ ከተጠየቅን ደግሞ በሶማሊያ ላይ የሚፈጸም የሉዓላዊነት እና ግዛት አንድነት ጥቃትን ለመመከት ድጋፍ እናደርጋለን" ሲሉም በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ቻይና፣ ህብረት፣አፍሪካ ህብረት እና ሌሎች ሀገራት ለሶማሊያ ሉዓላዊነት ድጋፍ እንደሚሰጡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ እና ሶማሊያም አለመግባባታቸውን በውይይት እንዲፈቱ የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ጥሪ ያቀረቡ ቢሆንም ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች በቀር ለውይይት እንደማይቀመጡ በኡጋንዳ በተካሄደው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ በሰጠችው መግለጫ በስምምነቱ ምክንያት የማንኛውም ሀገር ሉዓላዊነት አለመጣሱን እና ሌሎች ሀገራት በቀይ ባህር እና አካባቢው ያደረጉትን ብቻ ማድረጓን ገልጻለች፡፡