በአማራ ክልል ህጋዊነትን ያልተከተሉ እስሮች በአፋጣኝ ሊቆሙ ይገባል- ኢሰመኮ
ኮሚሽኑ በትጥቅ ግጭት ወቅትም ቢሆን ሲቪል ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚያበቃ በቂ ሕጋዊ ምክንያት መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል
ማንኛውም አካል በሲቪል ሰዎች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከማድረስ እንዲቆጠብ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል የሰበአዊ መብቶች ድንጋጌዎችን እና መርሖዎችን ያልተከተሉ እስሮች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ጠየቀ፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጎንደር እና ባሕር ዳር ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በአዲስ መልክ የበርካታ ሰዎች እስር እየተፈጸመ ነው ብሏል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና የሚዲያ እና የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ወደ ጊዜያዊ ማቆያዎች እየተወሰዱ መሆኑን ፤እስሮቹ በሕግ አግባብ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ያልተፈጸሙ መሆናቸውንም በመግለጫው ላይ አካቷል፡፡
በተጨማሪም በመንግስት የጸጥታ አካላት የተያዙ ተጠርጣሪዎቹ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ መሆናቸው እንዲሁም ከመካከላቸው ቋሚ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች እንደሚገኙበት ተገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ጉዳዩን በተመለከተ የሚያደርገውን ክትትል እንደሚቀጥል አስታውቆ በማንኛውም ሁኔታ የሚፈጸም እስር ተገቢውን የሕግ እና የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ሊከተል የሚገባ መሆኑን አሳስቧል፡፡
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የሚፈጸሙት እስሮች በታሳሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ አሉታዊ ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም “በትጥቅ ግጭት እና በጸጥታ መደፍረስ ወቅትም ቢሆን ሲቪል ሰዎችን ለመያዝ የሚያበቃ/በወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ በቂ ሕጋዊ ምክንያት መኖሩን፣ የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው በፍርድ ቤት የተሰጠ የመያዣና የብርበራ ትእዛዝ መኖሩን ማረጋገጥ ይገባል” ነው ያሉት፡፡
በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች በመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ብቻ እና መብቶቻቸውን ባከበረ ሁኔታ መያዛቸውን እንዲሁም በተያዙ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
መስከረም 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘውን አድቬንቲስት ትምህርት ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የከተማው አካባቢዎች ላይ ለጊዜው ማንነታችው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙት የቦንብ ፍንዳታዎች ያደረሱትን የሰብአዊ ጉዳት ኮሚሽኑ እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም አካል በሲቪል ሰዎች እና በሲቪል ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከማድረስ እንዲሁም የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሚያውክ ተግባር ሊቆጠብ እንደሚገባ ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአማራ ክልል፣ በፌደራል መንግስት የጸጥታ ኃይሎች እና በፈኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ግጭት 17 ወራት ያለፉት ሲሆን ግጭቱ አሁንም አልቆመም።
በግጭቱ አውድ ከእስራት ባለፈ መጠነሰፊ የሀብት ውድመት እና የንጹሃን ግድያዎች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ኢሰመኮን ጨምሮ በርካቴ የመብት ተሟጋች ተቋማት ሲፖርት አውጥተዋል።
በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በክልሉ መምህራንን ጨምሮ ሰዎች በጅምላ እየታሱ መሆኑን ገልጾ፣ እስሩ ሊቆም ይገባል ሲል አሳስቦ ነበር።
በቅርቡ የመከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ መንግስት በክልሉ ያለውን ችግር በውይይት ለመፍታት ያደረጠው ጥረት ስላልተሳካለት፣ በታጣቂዎች ላይ አዲስ ዘመቻ መጀመሩ ተናግረዋል።