ሄዝቦላ በእስራኤሏ የሀይፋ ከተማ ላይ ጥቃት አደረሰ
ሄዝቦላ ያስወነጨፈው ሮኬት በእስራኤል በትልቅነቷ ሶስተኛ የሆነችውን የሀይፋ ከተማ መምታቱን ፖሊስ በዛሬው እለት አስታውቋል
ሄዝቦላ በደቡባዊ ሀይፋ የሚገኝ ወታደራዊ ሰፈርን "ፋዲ 1" በተባለ ሚሳይል ኢላማ ማድረጉን ገልጿል
ሄዝቦላ ያስወነጨፈው ሮኬት በእስራኤል በትልቅነቷ ሶስተኛ የሆነችውን የሀይፋ ከተማ መምታቱን ፖሊስ በዛሬው እለት አስታውቋል።
ወደ መካከለኛው ምስራቅ በተስፋፋው የጋዛው ጦርነት የመጀመሪያ መታሰቢያ እለት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተቃጣ ጥቃት 10 ሰዎች መቁሰላቸውን ሮይተረስ የእስራኤል መገናኛ ብዙኻን ጠቅሶ ዘግቧል።
በኢራን የሚደገፈው እና የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋር የሆነው ሄዝቦላ በደቡባዊ ሀይፋ የሚገኝ ወታደራዊ ሰፈርን "ፋዲ 1" በተባለ ሚሳይል ኢላማ ማድረጉን ገልጿል።
እንደዘገባው ከሆነ ሁለት ሮኬቶች በእስራኤል
የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ የምትገኘውን ሀይፋ ከተማ የመቱ ሲሆን አምስቱ ደግሞ በ65 ኪሎሜትር ርቀው ቲበሪያስ ላይ አርፏል።
ፖሊስ እንደገለጸው በጥቃቱ የተወሰኑ ህንጻዎች የወደሙ ሲሆን በሰዎች ላይም ጉዳት ደርሶ የተወሰኑ ሰዎች በቅርቡ ወዳሉ ሆስፒታሎች ተወስደዋል።
የእስራኤል ጦር፣ የስለላ መረጃ መሰብሰቢያ ቁሳቁሶችን፣ የእዝ ማዕከላትን እና ሌሎች መሰረተልማቶችን ጨምሮ በቤይሩት የሚገኘውን የሄዝቦላን የስለላ ዋና መቀመጫ በጄት ማውደሙን ገልጿል። ጦሩ እንዳለው ባለፉት ሰአታት በቤይሩት አካባቢ የሚገኙ የሄዝቦላ የመሳሪያ ማከማቻዎችን መትቷል።
ከዚህ በተጨማሪም ጦሩ በደቡብ ሊባኖስ እና በበቃ የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን ጨምሮ የሄዝቦላ ኢላማዎችን መትቻለሁ ብሏል።
እስራኤል ሄዝቦላ ሆነብሎ የማዛዣ ጣቢያዎቹን እና የጦር መሳሪያ መጋዘኑን መኖሪያ ቤቶች ስር አደርጓል የሚል ክስ አቅርበዋል።
እስራኤል በዛሬው እለት ሀማስ ያደረሰባትን ያልተጠበቀ ጥቃት እና ከባድ ጥቃት የፈጸሙበትን አንደኛ አመት እያከበረች ነው።
እስራኤል የጥቃቱን አንደኛ አመት አስመልክቶ ሊቃጣባት የሚችል ጥቃትን ለመመከት ከፍተኛ የደህንነት ዝግጅት ያደረገች ሲሆን ጥቃቱን ለማሰብ ውስን መርሃግብር እንደሚኖር ተገልጿል።
ሀማስ የእስራኤል ድንበር ጥሶ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎችን ገድሎ፣ ሌሎች 251 የሚሆኑትን ደግሞ አግቶ መውሰዱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ እስራኤል በፈጸመችው መጠነሰፊ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት 42ሺ በላይ ፍስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
አንድ አመት ያስቆጠረው አሁን የቀጠለ ቢሆንም እስራኤል አሁን ላይ ዋና ትኩረቷን ወደ ሰሜን በማዞር ከሄዝቦላ ጋር እየተዋጋች ነው።