በመተሃራ ባጋጠመ የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመሬት ንዝረት አጋጠመ
አደጋው በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ አቅም እንደሌለው ነዋሪዎች ተናግረዋል
4 ነጥብ 9 ሬክተር ስኬል የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ መተሃራ አካባቢ ማጋጠሙን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የከርሰ ምድር ጥናት ባለሙያው ተናግረዋል
በመተሃራ ባጋጠመ የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመሬት ንዝረት አጋጠመ፡፡
ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት 2፡10 ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አነስተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ አጋጥሟል፡፡
እንደ ነዋሪዎች አስተያየት ከሆነ የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው በአዲስ አበባ በተለይም በሀያት፣ ሲኤምሲ፣ ቦሌ አራብሳ፣ የካ አባዶ ፣አዲሱ ገበያ እና ሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ተከስቷል፡፡
በሁኔታው የተደናገጡ ነዋሪዎችም ከቤታቸው ወደ ውጪ በመውጣት ተሰባስበው የታዩ ሲሆን በክስተቱ የተወሰኑ መደናገጦች እንደነበሩም ታዝበናል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ በኦሮሚያ፣አማራ እና አፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ማጋጠሙን ከነዋሪዎች ሰምተናል፡፡
ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አንድ የቦሌ አራብሳ ነዋሪ እንዳለችው “ቤት ውስጥ የተቀመጥንበት ሶፋ ለተወሰኑ ሰከንዶች ተንቀጥቅጧል” ስትል በወቅቱ ያጋጠማትን ነግራላነች፡፡
በሸዋ ሮቢት ከተማ የሚኖሩት አቶ በላይነህ ማሞ ለአል-ዐይን ስለ ክስተቱ ሲናገሩ “መሬት ፍራሽ ላይ ጋደም ብዬ ነበር፣ የቤቱ ጣሪያ በድንገት ሲንቀጠቀጥ ሳይ የማደርገው ጠፍቶኝ ደንግጬ ቁጭ አልኩ ወዲያው ደግሞ መንቀጥቀጡ ቆመ” ሲሉ ነግረውናል፡፡
ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በአብዛኛው በኦሮሚያ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ባሉ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ መከሰቱን አል-ዐይን ከነዋሪዎች ሰምቷል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ዳይሬክተር ዶክተር ኤልያስ ሌዊ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ "እስካሁን ባለው መረጃ እዚህ የመሬት መንቀጥቀጡ እዚህ አዲስ አባባ የተከሰተ ሳይሆን አዋሽ አካባቢ የተከሰተ ነው" ብለዋል።
ዶክተር ኤልያስ አክለውም በመሬት ውስጥ አልፎ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ልዩ ልዩ ቦታዎች መሰማቱን ገልጸው አደጋው እዚህ አዲስ አበባ የተከሰተ ሳይሆን ንዝረቱ በመሬት ውስጥ ተጉዞ መጥቶ እዚህ ያሉ ህንጻዎችን ማንቀጥቀጡን ተናግረዋል።
አደጋው በሪክተር ስኬል 4.9 መመዝገቡን የተናገሩት ዶክተር ኤልያስ ይሄም መተሃራ አካባቢ ካለው ፈንታሌ ተራራ አካባቢ የተከሰተ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ኮሙንኬሽን የዶክተር ኤልያስ ሌዊ አስተያየት ጋር የተቀራረበ መግለጫ ከደቂቃዎች በፊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አጋርቷል፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች እያጋጠሙ ሲሆን አደጋዎቹ የከፋ ጉዳት አላደረሱም፡፡
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ለይ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን፣ ሲዳማ፣ አማራ ክልል ደሴ አካባቢ እና ሌሎችም ስፍራዎች ባጋጠሙ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ከ500 በላይ ዜጎች ህይወት እና ንብረት ውድመት አደጋ ማጋጠሙ ይታወሳል፡፡