የታሰሩ የሚዲያ ባለሙያዎች "በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳሰበ
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ማህበር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ መንግስት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን እስር እና እንግልት እንዲያቆም ጠይቋል
ኢሰመኮ በአንድ ወር ወሰጥ በርካታ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንም ጠቅሷል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች (የሚዲያ ባለሙያዎች) የታሰሩበት መንገድ የህግ አግባብ እንደሌለው ገልጿል።
በሚዲያ አማካኝነት በሚፈጸም ወንጀል የተጠረጠሩ ባለሙያዎቹ በእስር እንዲቆዩ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በአቃቤ ህግ በኩል ለፍርድ ቤት መቅረብ ይችላል የሚለውን የሚዲያ አዋጅ የጠቀሰው ኢሰመኮ እስሩ ተገቢ አይደለም ብሏል።
"... በሚዲያ ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር" መለቀቅ አለባቸው ሲል አሳስቧል።
ኢሰመኮ በአንድ ወር ወሰጥ በርካታ ጋዜጠኞች መታሰራቸውንም ጠቅሷል።
"በዚህ ወር ውስጥ ብቻ ከታሰሩ የሚዲያ አባላት መካከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ጨምሮ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው ፣ ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ፣ ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ፣ ጋዜጠኛ በየነ ወልዴ ፣ ጋዜጠኛ ሰናይት አያሌው፣ ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ እንዲሁም በማኅበረሰብ አንቂነት እና በሚዲያ ሥራም የሚታወቁት መስከረም አበራ" እንደሚገኙበት ገልጿል።
ከታሰሩት መካከል "ተገቢ ላልሆነ አያያዝ የተዳረጉ፣ ከፊሎች ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው የነበሩ እና፣ ከፊሎችም ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ ናቸው" ብሏል ኢሰመኮ።
ኢሰመኮ ከሚዲያ ባለሙያዎች በተጨማሪ በፖለቲካ መሪዎች እና አባላት ላይ የሚደርሰው እስር እና ወከባም በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገልጿል።
በኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራሮችና ሌሎችም ላይ እስር እና እንግልት መድረሱን የገለጸው ኢሰመኮ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ በሆኑት እናት ፓርቲ፣ በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ እና የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ" ላይ እስር እና ማዋከብ ደርሶባቸዋል ብሏል።
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጵእኖ እንዳያሳድር መንግስት "በፖለቲካ ፖርቲ አባላትና አመራሮች፣ በሚዲያ አባላትና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ እሰር እንዲቆጠብ" ኢሰመኮ ጠይቋል።
"በወንጀል የተጠረጠሩና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሁኔታም በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ" መፈጸም አለበት ብሏል ኢሰመኮ።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ማህበር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ መንግስት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን እስር እና እንግልት እንዲያቆም ጠይቋል።
ከታሰሩት ጋዜጠኞች ውስጥ የተወሰኑት ያሉበት ቦታ እና ምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንኳን ቤተሰቦቻቸውም በቂ መረጃ የላቸውም ብሏል ማህበሩ።
ጋዜጠኞች ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ እየታሰሩ፣ እየታፈኑና ቤታቸውና ቢሯቸው እየተበረበረ መሆኑ ባለሞያዎች ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ፤ የፕረስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ ማድረጉንም ማህበሩ ገልጿል።