ኢሰመኮ በጋምቤላ ከተማ በሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረው ዛቻና ጥቃት ተቀባይነት የለውም አለ
ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳናኤል ድረጊቱ በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል ነው ብለዋል
ኢሰመኮ መስከረም 18 ባወጣው ሪፖርት በጋምቤላ በነበረው ግጭት ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች መገደላቸው ገለጾ ነበር
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ወይም መንግስት ኦነግ ሸኔ በሚለው እና በጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ በታጣቂዎቹ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች የደረሰውን የመብት ጥሰት የምርመራ ሪፖርት ባለፈው መስከረም ወር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ ከሰኔ 20 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ምርመራ ካደረገ በኋላ ባቀረበው ሪፖርት ኦነግ ሸኔ፣ ጋነግ፣የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች የተፈጸመውን ግድያ እና ዘረፋ ሲመሩ እና ሲያስፈጽሙ ነበር ብሏል፡፡
በጋምቤላ ከተማ“የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እና መሳሪያ በቤታችሁ እንዳለ ተጠቁመናል፤ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ” የአእምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን እና ቢያንስ 25 መቁሰላቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ሪፖርቱን ማቅረቡን ተከትሎ በክልሉ እየተስተዋሉ ያሉ ድርጊቶች ያሳስቡኛል ብሏል፡፡
ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ በማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ፣አነሳሽ እና ዛቻ ያዘሉ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ በኢሰመኮ ሰራተኞች ላይም የጥላቻ መልእክቶች ሲዘዋወሩ ማስተዋሉን ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ እንደገለጸው “መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመሄድ የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን መፈጸማቸውንና በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ” አድርሰዋል ብሏል፡፡
ኢሰመኮ እንደገለጸው በከተማዋ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ስራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ጥፋት ደርሷል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ድረጊቱ ተቃባይነት የሌለው በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽኑ ምርመራ ሲሰራ የተለያዩ እክሎች የሚያጋጥሙት ቢሆንም በሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሰራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
በሰኔው የጋምቤላ ጥቃት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው አሁንም ፍትህ አለማግኘታቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ መንግስት የኢሰመኮን ምክረ ኃሳብ እንዲተገብር አሳስበዋል፡፡