በኦሮሚያ ክልል ከህግ ውጪ ነጻነታችንን ተነፍገናል ያሉ ሰዎችን አቤቱታ መቀበሉን ኢሰመኮ ገለጸ
ኢሰመኮ አቤቱታ አቅራቢዎች እና የመንግስት አካላት ፊት ለፊት ቀርበው የተከራከሩበት ግልጽ ምርመራ በአዳማ አካሂዷል
በመድረኩ ላይ ግለሰቦችና ባለግዴታዎች ተገኝተው አቤቱታ እና ክርክር ማድረጋቸው ተገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች ሰብዓዊ መብታችን ተነካ ያሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ባለግዴታዎች በአንድ መድረክ የተገኙበት የግልጽ መድረክ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡
የግልጽ የምርመራ መድረኩ ተጎጂዎች፣ ባለግዴታዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እልባት ለማስገኘት እና አስቀድሞ ለመከላከል የመፍትሔ ሐሳቦችን ያመላከተ እንደሆነ ኮሚሽኑ ለአል ዐይን በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ከሰሞኑ በአዳማ ከተማ አራተኛውን ግልጽ የምርመራ መድረክ ማካሄዱን የገለጸ ሲሆን በመድረኩ ላይ የዘፈቀደ እስር፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስር እና በእስር ወቅት ተከስተዋል ስለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የተጎጂዎችን እና ምስክሮችን አቤቱታዎች አድምጫለሁ ብሏል፡፡
በቀረቡ አቤቱታዎች ዙሪያ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተሰጡ ምላሾችን እንዳዳመጠም ኮሚሽኑ አክሏል።
ተመርጠው ከቀረቡት 18 አቤቱታዎች መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ እና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የታሰረን ሰው ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ የፍርድ ቤት የዋስትና መብት ትእዛዝ አለማክበር ይገኙበታል ተብሏል።
እንዲሁም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጸዳጃ እና ሕክምና የማግኘት መብትን አለማክበር እና ጭካኔ የተሞላበትና የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በቀረቡት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል እንደሆኑ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የግልጽ ምርመራ መድረክ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ስልት መሆኑ ይታወቃል።
አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ መድረክ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን የሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባሕርይ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም ያካትታል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በተካሄደው በዚህ የግልጽ ምርመራ መድረክ ላይ በክልሉ ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር ወይም የምርመራና ክትትል ግኝቶች ያሏቸው አካላት ይህንኑ እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት ገለጿል፡፡
በዚህም መሰረት መቀመጫውን በውጭ ሀገር ያደረገ Oromo Legacy Leadership & Advocacy Association/OLLAA የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የየበኩላቸውን መረጃዎችና ትንተናዎች በጽሑፍ፣ በአካል እና በበይነ መረብ አማካኝነት ለኮሚሽኑ አስገብተዋል ተብሏል፡፡
ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተን ደርሰንበታል ያሉትን መረጃዎች በመድረኩ አቅርበው የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እንዲያውሉና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል እና በተለያዩ ዞኖች በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽን እና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ለቀረቡት አቤቱታዎችና ተፈጽመዋል ስለተባሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የፍትሕ እና የጸጥታ ተቋማቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም ለመብት ጥሰቶቹ መነሻ ምክንያት የሆኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታም አስረድተዋል ነው የተባለው።