ቻይና እና አሜሪካ ከደቡብ ቻይና ባህር ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገቡ
የቻይና ጦር ለሁለተኛ ጊዜ የአሜሪካን የጦር መርከብ ከባህር ክልሉ ማባረሩን አስታውቋል
እየተጋጋለ የመጣው የሁለቱ ሀያላን ሀገራት የቃላት ጦርነት የቀጠናውን ውጥረት አባብሶታል
ቻይና እና አሜሪካ ከደቡብ ቻይና ባህር ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የቃላት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ተገለጸ።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ የጦር መርከብን በደቡብ ቻይና የውሃ ክልል ላይ መመልከቱን እና አባሮ ማስወጣቱን አስታውቋል።
ቤጂንግ "ሚለስ ዩኤስኤስ" የተባለ አውዳሚ ሚሳዔል የታጠቀ የአሜሪካ የጦር መርከብ የውሃ ግዛቴ ነው ወደምትለው ደቡባዊ ቻይና ባህር ፓርሰል ደሴት አካባቢ መግቱንም ገልጻለች።
አሜሪካ እና ቻይና በደቡብ ቻይና ባህር ወደ ፍጥጫ እና የቃላት ጦርነት ሲገቡ ያሳለፍነው አርብ ለሁለተኛ ቀን ሲሆን፣ ሁለቱ ሀያላን ሀገራት በደቡብ ቻይና ባህር አካባቢ ውጥረት እንዲነግስም አድርገዋል ነው የተባለው።
የቻይና ጦር ባሳለፍነው መጋቢት ወርም በደቡብ ቻይና ባህር ውስጥ በፓራሴል ደሴቶች ዙሪያ በህገ-ወጥ መንገድ ገባ ያለውን የአሜሪካን የጦር መርከብ ማባረሩን መግለጹ የደታወሳል።
የጦር ኃይሉ በመግለጫው ከመንግስት እውቅና ውጪ የፀረ ሚሳዔል መርከብ በቻይና ግዛት ውስጥ በህገ-ወጥ መንገድ ገብቷል ነበር ያለው።
የቻይና ደቡባዊ ዕዝ ቃል አቀባይ ቲያን ጁንሊ "የዕዙ ኃይሎች በማንኛውም ጊዜ በከፍተኛ ንቃት የሀገሪቱን ብሄራዊ ሉዓላዊነት እና ደህንነት ይጠብቃሉ” ብለዋል።
“በደቡብ ቻይና ባህር ሰላምና መረጋጋትን በቆራጥነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ይወስዳሉ" ሲሉም ማስጠንቀቃቸው ተነግሯል።
በቀጣናው በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መጥቷል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ቤጂንግ የግዛት ይገባኛል ጥያቄዋን ለማራመድ ስትፈልግና አሜሪካ በደቡብ ቻይና ባህርና በታይዋን የባህር ዳርቻ ላይ ያላትን አቋም ለመቃወም በእስያ-ፓሲፊክ ትብብሮችን ስትፈጥር ቆይታለች።