በወልቂጤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት የከፈቱ የጸጥታ ሀይሎች እንዲጠየቁ ኢሰመኮ አሳሰበ
በወልቂጤ ከተማ የውሀ ችግራቸው እንዲፈታ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ ሳሉ የደቡብ ክልል ልዩ ሀይል ተኩስ ከፍቶባቸዋል ተብሏል
የደቡብ ክልል ፖሊስ ሶስት ሰዎችን ጭንቅላታቸውን እና ደረታቸውን መትቶ ሲገድል ከ30 በላይ ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል
በወልቂጤ ያልተመጣጠነ ኃይል በመጠቀም በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት የከፈቱ የጸጥታ ሀይሎች እንዲጠየቁ ኢሰመኮ አሳብቧል።
የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች የቧንቧ ውሃ አቅርቦት ከወር በላይ ለሆነ ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ ላጋጠማቸው የውሃ ችግር መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ለማቅረብ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ ፖሊስ ያልተመጣጠነ እርምጃ እንደተወሰደ ተገልጿል።
ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የክልሉ ፖሊስ በወሰደው የኃይል እርምጃ በነዋሪዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡
ኢሰመኮ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር አሰባሰብኩት ባለው መረጃ እና ማስረጃ መሠረት 3 ሰዎች ጭንቅላታቸውና ደረታቸው ላይ በጥይት ተመተው እንደተገደሉ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
እንዲሁም ቢያንስ በ30 ሰዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት መድረሱንም ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁም ብላል።
የአካባቢው ባለሥልጣናት በበኩላቸው ለደረሰው ጉዳት ምክንያት የሆነው ከሰልፈኞች ውስጥ የተወሰኑት ሰዎች በከተማው የውሃ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ላይ ድንጋይ መወርወራቸውን እና የመኪና መንገድ መዝጋታቸውን ተከትሎ በክልሉ ፖሊስ በተወሰደ የኃይል እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል ተብሏል፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተወሰደው የኃይል እርምጃ ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ተመጣጣኝ ያልሆነ መሆኑን ገልጸው “አንገብጋቢ በሆነ የውሃ አቅርቦት ጥያቄ ሰልፍ ወጥተው ድንጋይ በወረወሩና መንገድ በዘጉ ሰዎች ላይ ሕይወት የሚያጠፋ መሣሪያ ተጠቅሞና ጥይት ተተኩሶ ነዋሪዎች መገደላቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የክልሉ መንግሥት አስቸኳይ ማጣራት አድርጎ በአጥፊዎች ላይ ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እና የተጎዱ ሰዎችም ተገቢውን ካሳ ሊያገኙ ይገባል” ብለዋል ኮሚሽነቱ፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ለወደፊቱም ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ለጸጥታ ኃይሎች ግልጽ አመራር እንዲተላለፍ እና ቱጠያቂነትን ሜስፈን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
በደቡብ ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ከክልልነት አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ዞኑ አሁን ላይ በኮማንድ ፖስት ስር ሆኖ ይገኛል።