የኦሮሚያ ክልል ያለበቂ ማጣራት ህጋዊ ቤቶችን እያፈረሰ መሆኑን ኢሰመኮ ገለጸ
ኢሰመኮ በምርመራው ሸገር ከተማ አስተዳድር ተገቢውን ካሳ እና ማጣራት ሳያከናውን ዜጎችን ቤት አልባ እያደረገ መሆኑን ገልጿል
ኮሚሽኑ ምርመራ ካደረገባቸው አካባቢዎች መካከል ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸው
የኦሮሚያ ክልል ያለበቂ ማጣራት ህጋዊ ቤቶችን እያፈረሰ እንደሆነ ኢሰመኮ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት እየተከናወነባቸው ባሉ አካባቢዎች ምርመራ ማካሄዱን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ምርመራ ካደረገባቸው አካባቢዎች መካከል ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎች ዋነኞቹ ናቸው
ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በግል እና በቡድን ለኮሚሽኑ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ቅሬታውን ተከትሎ የመስክ ምልከታ በማድረግ መረጃ እና ማስረጃ ሰብስቤያለሁም ብሏል።
ኢሰመኮ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሰዎች በየአካባቢው ከቀድሞ/ነባር ባለ ይዞታዎች ቦታ ወይም ቤት በመግዛት ኑሮ መሥርተው ሲኖሩ የነበሩ መሆናቸውን፣ በየአካባቢው ከሚገኙ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የውሃ እና የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩ መሆናቸውን፣ ለተለያዩ የአካባቢው የልማት ሥራዎች እንደ ማንኛውም ማኅበረሰብ ክፍያዎችን ሲከፍሉ መቆየታቸውን እንዳስረዱት ገልጿል።
የሸገር ከተማ ኃላፊዎች በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ እንደ አዲስ መመሥረቱን ተከትሎ “ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸውን” ግንባታዎች በማፍረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸውልኛል ብሏል ኢሰመኮ፡፡
እንዲሁም የአየር ካርታን ጨምሮ ሕጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው፣ ከነባር የአርሶ አደር ይዞታ ውጪ የሆኑ እና በተለይም ከ2005 ዓ.ም በኋላ የተገነቡ ቤቶች እንዲፈርሱ በተወሰነው መሠረት የተከናወነ መሆኑን፣ ቤቶቹን የማፍረስ ሂደቱን በተመለከተም ከቤቶቹ ባለቤቶች ጋር በክፍለ ከተማ፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ውውይይት ተደርጎ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረጉንም ከአስተዳድሩ መስማቱን ኮሚሽኑ አክሏል።
ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ በለገጣፎ ለገዳዲ ፣ በሰበታ አካባቢ ፉሪ እና ለቡ ተክለሃይማኖት እንዲሁም በቡራዩ ገፈርሳ ኖኖ አካባቢዎች በመዘዋወር ቀደም ሲል የፈረሱ እና የማፍረስ ተግባሩ እየተከናወነ የነበረባቸውን አካባቢዎች መመልከቱን በሪፖርቱ ገልጿል።
ኮሚሽኑበለገጣፎ ለገዳዲ ክፍለ ከተማ በመገኘት እየፈረሱ የነበሩ ቤቶችንም የተመለከተ ሲሆን በምልከታው የቤት ማፍረሱ በግዳጅ ማስነሳቱ በግብረ ኃይል እየተከናወነ እንደነበረ እና በቦታው ከፖሊስ፣ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት በተጨማሪ ሌሎች ዱላ የያዙ ሲቪል ሰዎች እንደነበሩም ተመልክቻለሁ ብላል።
የክትትልና የምርመራ ሥራው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም እስካሁን በተገኙት መረጃዎች እና ማስረጃዎች መሠረት የቤት ማፍረስ እና በግዳጅ የማንሳት እርምጃው ከሰብአዊ መብቶች አኳያ የታዩበትን ክፍተቶች እና ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች በተመለከተ ኢሰመኮ የሚከተለውን ይገልጻል፡፡
በዓለም አቀፍ ሕግ እና የሰብአዊ መብቶች መርሆች መሠረት በግዳጅ ማንሳት ማለት አንድን ሰው ወይም ቤተሰብ ወይም ማኅበረሰብ ከሚኖርበት ቤት ወይም ቦታ ላይ ያለ ፈቃዱ፣ አማራጭ መፍትሔ ሳይሰጠው ወይም ሕጋዊ ጥበቃ ሳይደረግለት በጊዜያዊነት ወይም በዘላቂነት በኃይል አስገድዶ ማንሳትን የሚመለከት ነው፡፡
የቤት ፈረሳውና በግዳጅ ማንሳቱ የሚመለከተው የከተማውን መሪ ዕቅድ በሚጥሱ እና የመንግሥት ይዞታን በመውረርና ከአርሶ አደሩ ጋር በተደረገ ሕገወጥ የመሬት ግብይት የተገኙ ይዞታዎች ላይ የተደረጉ ግንባታዎችን ነው ቢባልም ሁሉም ቤቶች ግን በተመሳሳይ ሥሪት ላይ የተመሠረቱ ባለመሆናቸው የሚገዛቸውም ሕጎች እና አሠራሮች በዚያው ልክ የተለያዩ ሊሆኑ ይገባ ነበር ብሏል ኮሚሽኑ።
ኢሰመኮ ባደረገው ክትትልና ምርመራ እየፈረሱ ያሉ ቤቶች በተለያየ አይነት ክፍል የሚመደቡ መሆናቸውን አክሏል።