የጸጥታ ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጭ ሆነብለው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በባህርዳር፣ ደብረብርሀን እና ፍኖተ ሰላም ንጹሀን ዜጎች በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ተብሏል
ኢሰመኮ በአማራ ክልል የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአንድ ወር ጊዜ በላይ እንዳይቆይ ማሳሰቡ ይታወሳል
በአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ሆነብለው ከህግ አግባብ ውጭ(ኤክትራ ጁዲሻል) በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን የሚያሳይ ተአማኒ መረጃ እንደደረሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር ሰላማዊ ሰዎች በመንገድ ላይ ወይም ከቤታቸው ውጭ መግደላቸውን እና የተወሰኑ ወጣቶች ደግሞ ኢላማ ተደርገው መደብደባቸውን እና መገደላቸውንም ገልጿል።
ኢሰመኮ በጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች ንጹሃን መጎዳታቸውን እንዲሁም በሽዋሮቢት የጸጥታ ኃይሎች ከህግ አግባብ ውጭ ሆነብለው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን የሚያስረዳ ተአማኒ መረጃ ደርሶኛል ብሏል። ኢሰመኮ ዝርዘር ሁኔታው ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልገው ገልጿል።
ተፋላሚ ሀይሎች ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ግጭቶችን እንዲያቆሙ፣ ለሰላማዊ ንግግር ስፍራ እንዲያመቻቹና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ አክሎም በአማራ ክልል ያለው ግጭት በሰብዓዊ መብቶች ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ እየተከታተለ መሆኑን ገልጾ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመደንገጉ በፊትና በኋላ ከአዲስ አበባና ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መረጃዎችን እከተቀበለ እንደሆነም አስታውቋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከባድ የመድፍ ተኩስ ጭምር ጥቅም ላይ የዋለባቸው ከፍተኛ ውግያዎች እየተካሄዱ መሆኑንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
ውጊያው ንጹሀን ዜጎችን ከጉዳት ባልጠበቀ መልኩ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተከትሎ ሰላማዊ ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነውም ብሏል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ መንገድ ለመዝጋት የሞከሩ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ጭምር መገደላቸውን ፣ እስር ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች መሰበራቸውን፤ የጦር መሣሪያዎችና ጥይቶች ከመዘረፋቸው ባለፈ በቅድመ ፍርድ ያሉ እና ታራሚዎችም አመልጠዋል ብላል፡፡
በአማራ ክልል መንግስት ስር ያሉ በተለያዩ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ አመራሮች መገደላቸውንም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
በተለያዩ አካባቢዎች እንደ ኤሌክትሪክ ሐይል፣ ውሃ፣ ባንክ፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሰልክ፣ ኢነንተርኔት ያሉ መሠረታዊ አገልገሎቶች መቋረጣቸው በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
በደብረ ብርሃን ከተማ ለሁለት ቀናት፣ በአራት ብዙ ህዝብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በተካሄደ ከፍተኛ ውጊያ በሆስፒታል፣ ቤተ ከርስቲያን፣ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በስራ ቦታዎች ያሉ ሰለማዊ ሰዎች በመድፍና ተኩስ ልውውጥ እንደተገደሉ ኢሰመኩ በመግለጫው ላይ ጠቅሳል።
ከደብረብርሃን በተጨማሪም በፍኖተ ሰላም እና ቡሬ ከተሞች በተፈጸሙ የአየር ላይ ጥቃቶች ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ ጥቃቱም በመኖሪያ ቤቶችና ሕዝብ በሚበዛበቸው ስፍራዎች መፈጸሙን ተከትሎ የጉዳት መጠኑ ከፍ ማለቱ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ እንዳለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ከአማራ ክልል ውጪ በአዲስ አበባ በሚኖሩ የአማራ ማንነት ባላቸው ሰዎች ላይም መፈጸማቸውን አክሏል።
በመሆኑም የፌደራሉ መንግስት የጅምላ እስርን እንዲያቆም፣ ከህግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ታሳሪዎችን እንዲጎበኙ እንዲፈቅድ ሲል አሳስባል።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት፣ አሜሪካ፣ ብሪታንያ እና በርካታ ሀገራት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እየተፈጸሙ ያሉ የጸጥታ ችግሮች እንዳሳሰባቸው መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም በአማራ ክልል በሚንስትሮች ምክር ቤት የተጣለው የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቆይታ ጊዜ እንዲያጥር አሳስባል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚንስትሮች ምክር ቤት የተጣለውን የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ ከአንድ ወር እንዳይረዝም ኮሚሽኑ ባሳለፍነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
የፌደራል መንግስት በክልሉ የህግ ማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን እና የተወሰኑ የክልሉ ከተሞች ወደቀደመ ሰላማቸው መመለሳቸውን መግለጹ ይታወሳል።