ኢሰመኮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል ብቻ እንዲገብና ከአንድ ወር በላይ እንዳይፈጸም ጠየቀ
ኮሚሽኑ በአዋጁ የሚታሰሩ ሰዎች የብሄር ማንነትን አነጣጥሮ እንዳይሆን መጤን አለበት ብሏል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊታችን ሰኞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሀምሌ 28፤ 2015 ዓ.ም በሚንስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዝርዝር ተመልክቶ ምክረ ሀሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መላኩን አስታውቋል።
የፊታችን ሰኞ በአዋጁ ላይ ለመምከርና ለመወሰን አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽኑን ምክረ ሀሳቦች በጥንቃቄ እንዲያጤን ጠይቋል።
- በአማራ ክልል በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ገለጸ
- በአማራ ክልል መከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በአዋጁ የተመለከቱ ክልከላዎችና ግዴታዎች፣ ለመንግሥት የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ስልጣን፣ የአዋጁ ከባቢያዊና የጊዜ ተፈጻሚነት ወሰን፣ የህዝብ ተወካዮች እና ዳኞች ያለመከሰስ መብትን ጨምሮ ሌሎችም ሊገደቡ ስለማይችሉ መብቶች ጥበቃ፤ በአጠቃላይ የአዋጁ እያንዳንዱ አንቀጾች ከጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ህጋዊነት አንጻር አንዲመረመሩ ብሏል።
አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በተከታታይ ቀናት በአማራ ክልል የነበረው ግጭ ተወግዶ መደበኛ እንቅስቃሴዎች በመጀመራቸው ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት የአዋጁን አስፈላጊነት፣ ከባቢያዊና የጊዜ ተፈጻሚነት ወሰንን በጥንቃቄ እንዲያጤን ምክር ለግሷል።
ኢሰመኮ የአዋጁን የጊዜ ተፈጻሚነት "ከአንድ ወር ወይም የተወሰኑ ሳምንታት የበለጠ እንዳይሆን" ብሏል።
ተፈጻሚነቱም በጠቅላላ ሀገሪቱ ይልቅ ልዩ አደጋው ተከስቷል በተባለበት ቦታ [አማራ ክልል] ብቻ የተገደበ እንዲሆን ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።
ከእዚህ ቀደም በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ኢሰብአዊ አያያዞች፣ በተለይም በጥቆማ ላይ የተመሰረቱ እስሮችን በተመለከተ የጥቆማዎቹ መነሻ የሰዎቹ የብሔር ማንነት አለመሆኑን ለማረጋገጥ እና ምክንያታዊ ጥርጣሬ ስለመኖሩ ለማጣራት በቂ ጥረት ያልተደረገባቸው በርካታ እስሮች እንደነበሩ ጠቅሷል።