በአማራ ክልል በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ ገለጸ
በአንዳንድ አካባቢዎች የትራንስፖርትና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውንም ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል
ኢሰመኮ ሁሉም ወገኖች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡ አሳስቧል
በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ የንጹሃን ዜጎችን መብት በማይጥስና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ እንዲሆን ኢሰመኮ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል።
ኮሚሽኑ ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እየተባባሰ የመጣውን የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭትና የጸጥታ ችግር እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ሲከታተል መቆየቱን በመግለጫው አንስቷል።
የጸጥታ ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ እየተባባሰ በመምጣቱ ብዙ የክልሉ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ መሆናቸውን ያነሳው ኢሰመኮ፥ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና ሲቪል ሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አመላክቷል።
የትራንስፖርት እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውንና በቅርቡም የኢንተርኔት አገልግሎት በብዙ የክልሉ አካባቢዎች መቋረጡን ነው የገለጸው።
ነዋሪዎች በነጻነት ለመንቀሳቀስና ሥራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የእንቅስቃሴ ገደቦች መጣላቸውንም አስታውቋል።
ግጭቱ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ፣ ከጎረቤት ሀገራት ግጭት በመሸሽ የተሰደዱ በክልሉ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችንም ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ ነው ብሏል።
ሁሉም ወገኖች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡ የጠየቀው ኢሰመኮ፥ የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ነዋሪዎችን ለበለጠ ጉዳት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይዳርጉ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።
ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዕውቅና ያገኙ ሰብአዊ መብቶችንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርሆችን ባከበረና በማናቸውም ሁኔታ የማይገደቡ መብቶችን በጠበቀ አኳኋን እንዲፈጸም ጠይቋል።
አዋጁ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መሆን መርሖችን ባከበረ መልኩ እንዲተገበርም ነው ያሳሰበው።