አማራ ክልል ውስጥ ባለው ግጭት ህወሓት ተሳትፏል የሚባለው "በሬ ወለደ ጩኸት" ነው- የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፅንፈኛ ያላቸውን ኃይሎች በስም አልጠቀሰም
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአማራ ክልል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ተሳትፏል የሚባለው ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል
መንግስት በአማራ ክልል እየወሰደ ባለው እርምጃ "ህወሓት" ተሳትፏል የሚባለው "በሬ ወለደ ጩኸት" ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአማራ ክልል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ህወሓት ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ተሳትፏል የሚባለው ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል።
ጊዜያዊ አስዳደሩ በክልሉ ከፌደራል መንግስት ጋር ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል ያላቸው አካላት እየደረሰባቸው ያለውን ሽንፈት ለመሸፈን "የህወሓት ቀጥተኛ ተሳትፎ አለበት" የሚል "በሬ ወለደ ጩኸት" እያሰሙ ነው ብሏል።
በአማራ ክልል የሚገኙ "ፅንፈኞች እና አጋሮቻቸው በትግራይ ላይ አስበውት የነበረውን የጥፋት አላማ የፕሪቶሪያው ስምምነት" አክሽፎባቸዋል ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ "ፀረ- ፕሪቶሪያ እና ፀረ ትግራይ" አቋም በማራመድ ላይ ናቸው ሲል ይከሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፅንፈኛ ያላቸውን ኃይሎች በስም አልጠቀሰም።
"የፌደራል መንግስት በእነዚህ ኃይሎች ላይ እየወሰዳቸው ላሉ እርምጃዎች የትግራይም ሆነ የሌላ ወገን ድጋፍ ያስፈልገዋል ብለን አናምንም" ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ እንደሚፈልግ እና የፕሪቶሪያው ስምምነት "በፅንፈኛ ኃይሎች" እንዳይፈርስ ለማድረግ ከፌደራል መንግስት ጋር እንደሚተባበር ግልጽ አድርጓል።
በትግራይ የተጀመረው ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ነበር የተቋጨው።
በኘሪቶሪያው ስምምነት በአማራ እና ትግራይ ክልል ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ወይም ኮንቴስትድ ቦታዎች የተሰኙ ሲሆን በእነዚህ ቦታዎች ላይ እስካሁን ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
በአማራ ክልል፣ ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ በደረሰው ውሳኔ ሳቢያ የተነሳው ተቃውሞ ያስከተለው የጸጥታ ችግር በዚህ ሳምንት ተባብሷል።
በክልሉ የተነሳውን አለመረጋጋት በመደበኛ የጸጥታ መዋቅር መፍታት አልተቻለኝም ያለው መንግስትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አውጇል።
በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተቀሰቀው ግጭት ንጹሃን ሰዎች እንዲጎዱ እና የሀገር አቋራጭ ትራንፖርት እንዲስተጓጎል አድርጓል።
የተመድ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተባባሰ የመጣው ሁኔታ በጽኑ እንደሚያሳስበው ገልጿል።