ኦነግ ሸኔ በምስራቅ ወለጋ ዞን 50 ተፈናቃዮችን መግደሉን ኢሰመኮ ገለጸ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ፥ በኦሮሚያ ክልል የዜጎች ደህንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል
ኮሚሽኑ መንግሥት በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለሚፈጸምበት የኦሮሚያ ክልል ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቋል
በኦሮሚያ ክልል የዜጎች ደህንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ኢሰመኮ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ አኖ ከተማ በሚኖሩ ተፈናቃዮች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ በጥር 25 ቀን 2015 ዓ.ም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ኢላማ በማድረግ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በምርመራዬ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በተጠቀሰው ዕለት ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው የወታደር ልብስ የለበሱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) መሆናቸው በነዋሪዎች የተገለጹ ታጣቂዎች በሦስት አቅጣጫ ወደ አኖ ከተማ ገብተው በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያና የአካል ጉዳት፣ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት አድርሰዋል ነው ያለው ኮሚሽኑ በመግለጫው።
- "አዲስ ሲኖዶስ" በሚል የተቋቋመው አካል በኃላፊዎች ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል ቤተክርስቲያናትን መቆጣጠሩን ኢሰመኮ ገለጸ
- በኦሮሚያ ክልል"ግጭቶችና ጥቃቶች"የሚከሰቱባቸው ቦታዎች መጨመራቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በጥቃቱ ዋና ኢላማ የተደረጉት ከጎቡ ሰዮ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መሆናቸውንም ኢሰመኮ በምርመራው ማረጋገጡን ገልጿል።
በከተማዋ ውስጥ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከ13 ቀበሌዎች ተፈናቅለው በአኖ ከተማ በመጠለያ ውስጥ እንዲሁም ከመጠለያውጭ ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ከ10 ሺህ 800 በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙም ነው ኮሚሽኑ ያስታወቀው።
በዚህ ከተማ በታጣቂዎቹ ጥቃት አንድ የክልል የሥራ ኃላፊ ከነሾፌሩ፣ የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሻ አባላትን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል ተብሏል።
ከሟቾች መካከልም 42 ተጎጂዎች በተፈናቃዮች የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ እና ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ይኖሩ የነበሩ ተፈናቃዮች እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ የተባሉ ነዋሪዎች እንደሚገኙበት ነው የተገለጸው።
ታጣቂዎቹ በከተማው ‘ሰኞ ገበያ’ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ ተፈናቃዮችን ቤት ለቤት እየዞሩ በተለይ የአማራ ብሔር ተወላጆችን ለይተው እንደገደሉም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ታጣቂዎቹ የአረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናት ተፈናቃዮች መጠለያነት ተቀይሮ በማገልገል ላይ ይገኝ የነበረ ግቢ ውስጥ በመግባት በፈጸሙት ጥቃት፤ በግቢው ውስጥ የነበሩ ማምለጥ ያልቻሉ ወንድ ተፈናቃዮችን መርጠው ከመግደላቸው ባለፈ ሬሳቸውን በእሳት እንዳቃጠሉ ተገልጿል።
በከተማው የነበረ ውስን የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ጥቃቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም ታጣቂዎቹ በቦታው ከነበረው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አንፃር በቁጥር እጅግ በርካታ በመሆናቸው እና ጥቃቱ በዕቅድና ዝግጅት የተፈጸመ በመሆኑ ምክንያት ተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ከነቀምቴ እስከ መጣበት እስከ እኩለ ቀን 6፡00 ሰዓት ድረስ ታጣቂዎቹ በከተማዋ እየተዘዋወሩ ግድያ እና ዘረፋ ፈጽመዋል ብሏል ኢሰመኮ በመግለጫው፡፡
በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት ከተማዋን መልሶ ከተቆጣጠረ በኋላ “ከሸኔጋር ተባብራችኋል” በሚል ጥርጣሬ ስምንት ወጣቶችን በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ዋነኛ ተጎጂ የሆኑት በተለያዩ መንገዶች ለጥቃት የተጋለጡ ሲቪል ሰዎች መሆናቸውን ኮሚሽኑ ለረጅም ጊዜ በግጭቱ ላይ እያደረገ ያለው የክትትል እና ምርመራ ግኝቶች ያሳያሉ” ብለዋል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት ያካሄዳቸው ምርመራዎች በኦሮሚያ ክልል የዜጎች ደህንነት የከፋ ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን ማመላከታቸውንም ነው ኮሚሽነሩ ያነሱት።
ኮሚሽኑ ሁሉም ወገኖች ሲቪል ሰዎችን እና የሲቪል ሰዎችን ንብረት የጥቃት ኢላማ ከማድረግ እንዲቆጠቡ፣ ለተፈጸሙ ጥቃቶችም መንግሥት የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ ጥሪ አቅርቧል።