በአዲስ አበባ ከአፋን ኦሮሞ ትምህርት እና መዝሙር ጋር በተያያዘ በህጉ መሰረት እንዲሰራ ኢሰመኮ አሳሰበ
ኢሰመኮ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ግልጽ እና አሳታፊ አሰራርን እንዲከተልም ምክረ ሀሳብ አቅርቧል
በአዲስ አበባ ከአፋን ኦሮሞ ትምህርት እና ከኦሮሚያ ክልል መዝሙርና ሰንደቅ አላማ ጋር በተያያዘ ሁከት ተከስቶ እንደነበር ይታወሳል
በአዲስ አበባ ከተማ ከአፋን ኦሮሞ ትምህርት እና መዝሙር ጋር በተያያዘ በህጉ መሰረት እንዲሰራ ኢሰመኮ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወይም ኢሰመኮ በአዲስ አበባ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል መዝሙር እና ሰንደቅ አላማ መሰቀል ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ሁከት አስመልክቶ ሪፖርት አውጥቷል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ እንዳለው በአዲስ አበባ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማን መስቀልና የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ውሳኔውን በሚቃወሙ እና በሚደግፉ ተማሪዎች መካከል ውዝግብና ግጭት መከሰቱን ገልጿል።
ኮሚሽኑ አደረኩት ባለው ምርመራና ክትትል የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን፣ መምህራን እና ኃላፊዎችን፣ በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የነበሩ ተማሪዎችንና ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም ማነጋገሩን ገልጿል።
የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች የነበሩ ምስክሮችንና የተማሪዎች ወላጆችን እንዲሁም የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሌሎች ኃላፊዎችን በማነጋገርና መረጃዎችና ማስረጃዎች ማሰባሰቡንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
በመሆኑም በቀጣይ ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደፊትም እንዳያጋጥሙ ለችግሩ መንስኤ ለሆነው የሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ውዝግብ ሕፃናትን ጨምሮ ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ግልጽ የሆነ የሕግ እና ፖሊሲ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ብሏል።
እንዲሁም መንግሥት አሁን በሥራ ላይ ያሉትን ሕጎች እና የሰብአዊ መብቶች መርሆችን በማክበርና በማስከበር የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በጋራ እንዲከላከሉ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የየትምህርት ቤቶቹና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሰላም፣ በመቻቻል እና የሃሳብ ልዩነትን በመቀበልና በሰላማዊ መንገድ ብቻ በመፍታት ላይ እንዲመሰረትም ኮሚሽኑ አሳስቧል።