"አዲስ ሲኖዶስ" በሚል የተቋቋመው አካል በኃላፊዎች ድጋፍ በኦሮሚያ ክልል ቤተክርስቲያናትን መቆጣጠሩን ኢሰመኮ ገለጸ
ኢሰመኮ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ሀይል ያልተመጣጠነ ሀይል መጠቀሙንም አስታውቋል
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ስምንት ሰዎችን እንደገድሉ ኢሰመኮ ገልጿል
አዲስ ሲኖዶስ" በሚል የተቋቋመው አካል በኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎች ድጋፍ ቤተ ክርስቲያናትን እንደተቆጣጠረ ኢሰመኮ ገለጸ።
ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሦስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት “የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ቤተ ክህነት” ተብሎ የሚጠራ አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን እና ለሃያ ስድስት የሃይማኖት አባቶች የጵጵስና ማዕረግ ሹመት መስጠታቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንግስት እየተነጋገረች መሆኑን አስታወቀች
ይሄንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ይህንኑ ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ሦስቱን ጳጳሳት ጨምሮ እነሱ የሾሟቸውን የሃያ ስድስት አባቶችን ማዕረግ በማንሳት ከቤተክርስቲያኗ በውግዘት እንዲለዩ መወሰኑ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ወይም ኢሰመኮ በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠሩ ያሉ ክስተቶችን በቅርበት መከታተሉን ገልጿል።
አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁት ጳጳሳት በአንዳንድ ቦታዎች በኃላፊዎች ድጋፍ ጭምር በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን መያዛቸውን ኮሚሽኑ በምርመራዬ አረጋግጫለሁ ብሏል።
እነዚሁ አካላት ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም የሻሸመኔ ደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያንን ለመያዝ ያደረጉትን እንቅስቃሴ ተከትሎ እርምጃውን ለመቃወም የወጡ ሰዎችን ለመበተን በመንግሥት ጸጥታ አባላት በተወሰደ ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ እና ከጸጥታ አባሎቹ ጋር ሲተባበሩ በነበሩ ሰዎች ቢያንስ ስምንት ሰዎች በጥይትና በድብደባ መገደላቻውን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ገልጿል።
ኢሰመኮ አክሎም ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ሰዎች ለተለያየ ዓይነትና መጠን የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ለተለያየ ጊዜ መጠን መታሰራቸውንም አስታውቋል።
በተለያዩ ቦታዎች አዲስ “ቤተ ክህነት” አቋቁመናል በማለት ያሳወቁትን ጳጳሳት በተቃወሙ ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች ላይ ድብደባ፣ ማዋከብ፣ ከቤተ ክርስቲያናት ማባረር፣ የመንቀሳቀስ መብትን በኃይል መገደብ እና ከሕግ ውጭ እስራት እንደተፈጸመም ኢሰመጉ ገልጻል።
እንዲሁም ሲኖዶሱ ከጥር 29 እስከ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. የሚታሰበውን የጾም ወቅት አስመልክቶ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ በተለያዩ ቦታዎች እስር፣ ወከባ፣ ከሥራ ቦታና አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ማግለል እንደተፈጸመ፣ እንዲሁም
የችግሩ ግዝፈት ቢለያይም በተለይ በነቀምቴ፣ በግምቢ፣ በደምቢ ዶሎ፣ በሻምቡ፣ በአሰላ፣ በሻሸመኔ፣ በጭሮ፣ በያቤሎ፣ በጅማ፣ በቡሌ ሆራ፣ እና በነጌሌ ቦረና ከተሞች ከሕግ ውጭ እስራትና ተመሳሳይ የማዋከብ ድርጊቶች እንደተፈጸ ታውቋልም ብሏል፡፡
በመንግሥት የጸጥታ አባሎች ተመጣጣኝ ባልሆነ ኃይል አጠቃቀም በጥይት እና በድብደባ የተፈጸሙ ግድያዎች፣ ከሕግ ውጭ የተፈጸሙ እስሮችና የእንቅስቃሴ ገደቦች፣ እንዲሁም ሲኖዶሱ ያቀረበውን የጥቁር መልበስ ጥሪ የተቀበሉ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ እስሮች፣ ከአገልግሎት እና ከሥራ ቦታ ማግለልና ማንገላታት ፍጹም ተገቢ ያልሆኑ እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ በነጻነት ሃይማኖታቸውን እና ሐሳባቸውን የመግለጽ ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን የሚፃረሩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው ሲል ኢሰመኮ አሳስቧል።
ስለሆነም መንግሥት የተሟላና ተገቢውን ማጣራት አድርጎ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ እና የተጎዱትንም ሊክስ ይገባል።
በተጨማሪም የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ኃይል ከመጠቀም፣ ከማንገላታት፣ ከሕገ ወጥ እስር እና የሰዎችን እንቅስቃሴ ያለበቂ ምክንያት ከመገደብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
በቤተክርስቲያ የተፈጠውን ችግር ለመፍታት በዛሬው እለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እየተወያዩ መሆናቸውን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች።