በቤኒንሻንጉል ካማሺ ዞን የሚገኘው የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ኢሰመኮ ገለፀ
በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው መሸሻቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል
ታጣቂ ቡድኑ ንብረቶችን ማቃጠሉ ፣ ነዋሪችን፣ አመራሮችን እና የመንግስት ሰራተኞችን መግደሉና ማገቱም ተገልጿል
በቤኒንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ ከማሺ ዞን የሚገኘውና ከሃያ አምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙበት የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ ከሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን የደረሱት መረጃዎች እንደሚያመለክቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለፀ።
በርካታ ነዋሪዎች፣ የወረዳው አስተዳደር እና ፖሊስ አካባቢውን ጥለው ወደ ተለያዩ ስፍራዎች መሸሻቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። ታጣቂ ቡድኑ የመንግስት እና የግለሰብ ንብረቶችን ማቃጠሉ፤ ነዋሪችን፣ የወረዳውን እና የዞን አመራሮችን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኞችን መግደሉ እና ማገቱም ተገልጿል።
ኢሰመኮ በመግለጫው እንዳለው ፣ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በአቅራቢያው ያለው የፀጥታ ኃይል ከአቅሙ በላይ እንደሆነና ተጨማሪየተላከው ኃይልም ወደ አካባቢው እንዳልደረሰ ይገልጻሉ።
ይህ ክስተት በክልሉ የቆየው የጸጥታ ችግር እየተባባሰና መልኩን እየቀየረ መምጣቱን የሚያሳይ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት የሚያሳድር ነው ብሏል ኮሚሽኑ።
ኢሰመኮ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ እና ከሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑንም ገልጿል።
ኮሚሽኑ መንግስት በአፋጣኝ የአካባቢው እና የክልሉን የፀጥታ ኃይል እንዲያጠናክርና እና ተጨማሪ የሰዎች ሞት እና የከፋ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳይከሰት እንዲከላከልም ጥሪውን አቅርቧል።