ፖለቲካ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በመተከል ለደረሰው ግድያና ውድመት ይቅርታ ጠየቀ
በቀጣይ የበወንጀል የተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል
'ብልፅግና አሀዳዊ ነው' በሚል ትርክት በሁለት አቋም ህዝብን ሲበድሉ የነበሩ አመራሮች መኖራቸውን ፓርቲው ገምግሟል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ በመተከል ዞን ለደረሰው ግድያና ውድመት ይቅርታ ጠየቀ።
የክልል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ጉባዔ ዛሬ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው ፓርቲው ይቅርታ መጠየቁ የተገለጸው፡፡
ጉባኤው በአሶሳ ከተማ በክልሉ ወቅታዊ የፖለቲካና የሠላም ሁኔታ ላይ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
በዚህም በክልሉ መተከል ዞን በደረሰው በማንነት ላይ ያተኮረ አሳዛኝና ዘግናኝ ግድያና ውድመት ፓርቲው ይቅርታ መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት “ብልፅግና አሀዳዊ ነው በሚል የሀሰት ትርክት” ሁለት ቦታ በመርገጥ ህዝብን ሲበድሉ የነበሩ አመራሮች መኖራቸውም ተገምግሟል፡፡
በቀጣይ የሕግ የበላይነትን በማስከበር በወንጀል የተሳተፉ የስራ ኃላፊዎችም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
የፓርቲውን እሴትና መርህ በማክበር የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ከጉባዔው በኋላ በወጣው የአቋም መግለጫ ተገልጿል።