ኢሰመኮ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ ያተኮረ ብሔራዊ ምርመራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ
ፕሮጀክት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ15 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የሚተገበር ነው
ፕሮጀክቱ በሁሉም ክልሎች ከሶስት እስከ ስድስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ይተገበራል ተብሏል
ኢሰመኮ ነፃነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ላይ ያተኮረ ብሔራዊ ምርመራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነጻነታቸውን በተነፈጉ ሰዎች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የምርመራ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
ይህ ፕሮጀክት ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ15 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን የህግ የበላይነት የሚሰፍንበትን መንገድ ማሳየት፣ በፍትህ አካላት መካከል በጋራ መስራት የሚችሉበትን መንገድ መፍጠር እና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማድረግ የዚህ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ አለማየሁ ተናግረዋል።
ብሄራዊ ምርመራው በሁሉም ክልሎች የሚተገበር ሲሆን ህጻናት፣ ያለ ክስ የታሰሩ ግለሰቦች፣ ታራሚዎች፣ ዩንቨርሲቲዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋልም ተብሏል።
ከ3 እስከ 6 ዓመታት ውስጥ ይተገበራል የተባለው ይህ ፕሮጀክት ተመሳሳይነት ያላቸውን የበርካታ ግለሰብ ጉዳዮችን አሳታፊ በሆነ መንገድ ለመፍታት እንደሚያስችል ፕሮጀክቱ ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል።
እንዲሁም ባለ መብቶችን እና ባለግዴታዎችን በአንድ መድረክ በውስብስብና ስልታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ማወያየትም ያስችላል ተብሏል።
ብሔራዊ ምርመራውን ለማካሄድም ከሚመለከታቸው የፍትህ እና የአስተዳድር ተቋማት ጋር በአጋርነት ለመስራት የሚያስችል እና መግባባትን የመፍጠር ስራዎች ጎን ለጎን በመከናወን ላይ እንዳሉም ተጠቅሷል።