ኢሰመኮ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በመንግስት የጸጥታ ኃይል ከተያዙ በኋላ በጥይት መገደላቸውን ገለጸ
ኢሰመኮ የተፈጸመው ግድያ ከህግ ውጭ እና አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ ነው ብሏል
ኢሰመኮ በሚችሌ የገዳ አባላት ላይ እና በፖሊስ አባላት የተፈጸመውን ወንጀል ማጣራትና ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል
ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል፣በምስራቅ ሽዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በህዳር ወር የተፈጸመውን ጥቃት ከታህሳስ 7 እስከ 12፣2014 ድረስ ያካሄደውን የምርመራ ውጤት ጥፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ባወጣው መግለጫ በምርመራው “ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በኅዳር 22 ቀን 2014 ዓ.ም. በመንግስት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደውና የፀጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት፣ ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመተው”መገደላቸውን ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ የተፈጸመው ግድያ ከህግ ውጭ እና አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ ነው ብሏል፡፡
ኢመመኮ ከተገደሉት “በተጨማሪ 23 የጅላ አባላት መካከል አንድ ሰው ሞጆ ከተማ በሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ስር እያለ” ህይወቱ ማለፉን ጠቅሷል፡፡
ህይወቱ ያለፈውን ሰው አስከሬን ምርመራ ሳይደረግ ቤተሰቦቹ ወስደው እንዲቀብሩት መደረጉ ከህግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ መካሄዱን አሳማኝ ያደርገዋል ብሏል ኢሰመኮ፡፡
ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ ከከረዩ የሚችሌ ገዳ አባልት ግድያ ቀደም ብሎ “…ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለስራ ወደ ፈንታሌ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሄደው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አከባቢ ወደ መተሃራ ከተማ በመመለስ ላይ የነበሩ የፀጥታ አባላት ላይ በወረዳው ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተፈጸመ ጥቃት የ11 ፖሊስ አባላት ሕይወት ማለፉና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሳለቸው” ገልጿል፡፡
መግለጫው በፖሊሶች ላይ የቃጣውን ጥቃት ተከትሎ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ወደ ፈንታሌ ወራዳ በከረዩ ሚችሌ አባገዳዎችና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር የደረሱ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር እንዲውሉ አድርገዋል ብሏል፡፡
ኢሰመኮ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባልት ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ያደረጉ የጸጥታና የአስተዳደር ላይ ምርመራ ተደርጎ ለህግ ሊቀርቡ ይገባል ብሏል ኢሰመኮ፡፡
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) በሚችሌ የገዳ አባላት ላይ እና በፖሊስ አባላት የተፈጸመውን ወንጀል ማጣራት እና በህግ ተጠያቂ ማደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡