ህወሓት ሰሜን ወሎና ደቡብ ጎንደር “ሆን ብሎ” ንብረት ማውደሙንና ሰው መግደሉን አረጋግጫለሁ- ኢሰመኮ
የህወሃት ታጣቂዎች በሲቭል ሰዎች ቅጥር ግቢ ውስጥ ምሽግ በመቆፈር ሰዎችን ለጉዳት ዳርገዋል-ኢሰመኮ
ኢሰመኮ በአማራና በአፋር ክልል ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ተፈጽሟል ያለውን ሰፊ ጾታዊ ጥቃት በተመለከተ ምርመራ እንደሚያካሂድ ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን( ኢሰመኮ) ባወጣው ሪፖርት የህወሓት ታጣዎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ንጹሃንን መግደላቸውንና ሆን ብለው የንብረት ዘረፋና ውድመት መፈጸማቸውን ማረጋገጡን አስታወቁ፡፡
ኢሰመኮ ከሐምሌ ወር 2013ዓ.ም ጀምሮ፣ የትግራይ ክልል የነበረው ግጭት ወደ አማራ ክልል መስፋፋቱን ተከትሎ የህወሃት ታጣቂዎች የፈጸሟቸውን የመብት ጥሰቶች ሪፖርት ዛሬ ይፋ አደርጓል፡፡
- ህወሓት በደብረታቦር በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው የተባሉ 5 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
- የአማራ ክልል መንግስት ህወሃት ወልዲያ ላይ በተኮሰው ከባድ መሳሪያ በንጹሀን ላይ ጉዳት ማድረሱን ገለጸ
ኢሰመኮ ምርመራ አካሂጄባቸዋለሁ ባላቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች በተደረገው ጦርነት በትንሹ 184 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል፡፡
ኢሰመኮ “…በርካታ ሰዎች የአካል ጉዳት እና የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተለይ የህወሓት ታጣቂዎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎችን ተኩሰው መግደላቸውንና ማቁሰላቸውን፣ ሰፊ የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ሆን ብለው መፈፀማቸውን አረጋግጧል፡፡”
ሪፖርቱ ህወሓት “በሲቪል ሰዎች መኖሪያ ቤቶች እና ቅጥር ግቢዎች ውስጥ ምሽግ በመቆፈር እና ከባድ መሳሪያዎችን በመተኮስ ሲቪል ዜጎችን በአጸፋ ለሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ጥቃት” አጋልጠዋል ብሏል፡፡
ኢሰመኮ የሲቪል ሰዎችን ቤት እንደ ምሽግ በመጠቀሙ፤ የበርካታ ሲቪል ሰዎች ሞት እና አካል ጉዳት እንዲከሰት እንዲሁም ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት የሕወሓት ታጣቂዎች ሲቪል ሰዎች የሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ ሆነው የሚፈፅሙበትን ጥቃት ለመከላከል እና ለማጥቃት ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀሙ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞትና አካል ጉዳት ደርሷል፤ ንብረትም እንዲወድም ሆኗል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በግጭቱ ተሳታፊዎች በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
በአማራና በአፋር ክልል ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ “መጠነ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰፊ የሆነ የጾታዊ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ መረጃዎች” እንዳሉ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በፌደራል መንግስት የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል አለመግባባት የተፈጠረው፤ ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲያስተዳድር የነበረው የገዥ ፓርቲ ግንባሮች በመዋሃድ ብልጽግና ፓርቲን ሲመሰርቱ ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ብሎ በማፈንገጡ ነው።
ህወሓት የፌደራል መንግስቱ ህገወጥ ነው ያለውን ምርጫ ማካሄዱም የአልመግባባቱ ጡዘት ውጤት ነበር።
በሁለቱ አካላት መካከል የነበረው አለመግባባት ወደ ወታራዊ ግጭት ያመራው፤ ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነበር፡፡
ክህደት ፈጽሟል ባለው ህወሓት ላይ “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በማወጅ የትግራይ ዋና ከተማና ብዙ ቦታዎችን መያዝ የቻለው መንግስት ከ8 ወራት በኋላ ለትግራይ ህዝብ የጽሞና ግዜ ለመስጠት በማሰብ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱ ይታወሳል።
በክልሉ በነበረው ጦርነት ወቅት ዜጎች መፈናቃላቸውንና መገደላቸውን ኢሰመኮና ሌሎች አለምአቀፍ ተቋማት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
መንግስት ጦሩን ከክልሉ ማስወጣቱን ተከትሎ፣ ሕወሓት ወደ አማራ አፋር ክልል በመግባት ጥቃት ከፍቷል፡፡
አሁን ጦርነት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ህዝብ ለርሃብና ለሞት አደጋ የተዳረገ ሲሆን በ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጦርነቱን በመሸሽ መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል መንግስት መቅርቡ ገልጿል፡፡
መንግስት በኢትዮጵያ በሽብር የተፈረጀው ህወሓት ደቅኖታል ያለውን ሉአላዊነትን ችግር ውስጥ የሚያስገባ አደጋ ለመቀልበስ ባለፈው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።
በአፍካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሰጉን ኦባሳንጆ፣ በኢትዮጵያ አንድ አመት ያስቆጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡