ኢሰመኮ በኬንያ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ጎበኘ
ፍልሰተኞቹ ሀገራቸው ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ ረገድ የህገወጥ ደላሎች ሚና ከፍተኛ ነው ተብሏል
በእስር ላይ ከሚገኙ ፍልሰተኞች እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙ ተገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኬንያ ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ጎበኘ፡፡
ወደ ኬንያ ለስራ ጉዳይ የተጓዘው የኢሰመኮ ቡድን፤ በኬንያዋ ዋጂር ከተማ የሚገኘውን የፖሊስ ማቆያ ጣቢያ የጎበኘ ሲሆን በማቆያ ጣብያው በእስር ላይ የሚገኙ 27 መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞችን መኖራቸው አረጋግጧል፡፡
በእስር ላይ ከሚገኙ ፍልሰተኞች 9 የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ሲሆን አራቱ ሴቶች መሆናቸውን ቡድኑ አስታውቋል፡፡
ህጻናቱ መደበኛ ላልሆነ የፍልሰት አዙሪት የተጋለጡና በህገወጥ ደላሎች እና በሙስና በተዘፈቁ ባለስልጣናት ምክንያት ሰብአዊ መብታቸው አደጋ ላይ የወደቀ ነውም ብሏል፡፡
ተመድ በየመን የታሰሩ 6 ሺ 750 ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው ሊመልስ ነው
በዋጅር ፖሊስ ጣቢያ ተይዞ የነበረና ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ የተወሰነበት አንድ አስፋው ተባለ የ17 ዓመት ኢትዮጵያዊ ፍልሰተኛ ማነጋገሩን የገለጸው ቡዱኑ፤ ፍልሰተኞቹ ሀገራቸው ጥለው እንዲሰደዱ በማድረግ ረገድ የህገወጥ ደላሎች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
ኢሰመኮ በድህረ ገጹ ላይ ባወጣው መረጃ፤ ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ የፍልሰተኞች አስተዳደር ለማስተዋወቅ በጎረቤት ሀገራት ከሚገኙ ብሄራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
ኬንያን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሀገራት የተሰደዱ በርካታ ኢትዮጵያውን ፍልሰተኞች እንዳሉ የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) መረጃ ያመለክታል፡፡
ድርጅቱ የጦርነት መነሃሪያ በሆነችው የመን የሚገኙ 6 ሺ 750 ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን በቅርቡ ወደ ሀገራቸው የመመለስ እቅድ እንዳለው ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡
ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ፍልሰተኞቹን ለመመለስ ላወጣው ዕቅዱ ድጋፍ የሚሆን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ያስፈልገኛል ማለቱም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡