ተፈናቃይ እና ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 111 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተባለ
ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ ድርጅቱ አስታውቋል
ባለፉት 8 ወራት ከ63 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከአረብ አገራት መመለሳቸውን ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገልጿል
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ተፈናቃይ እና ከስደት ተመላሽ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 111 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል አለ።
ድርጅቱ ለአል ዐይን ዜና በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ እና ከጎረቤት እና መካከለኛው ምስራቅ አገራት የተመለሱ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 111 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልጿል።
ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ከ63 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ወደ አገራቸው የተመለሱ ሲሆን ፣ “ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል” ብሏል ድርጅቱ።
በመሆኑም በተያዘው የፈረንጆቹ 2021 ዓመት ለእነዚህ ዜጎች የስነ ልቦና ፣ የህክምና ፣ የኢኮኖሚ እና ሌሎች ድጋፎችን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠይቋል።
ከዚህ ባለፈም ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ በአንበጣ መንጋ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚጎዱ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ማቀዱንም ድርጅቱ በመግለጫው ጠቁሟል።
ከ27 በላይ የዓለማችን አገራት 800 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞችም በኢትዮጵያ ተጠልለው ህይወታቸውን በመምራት ላይ ሲሆኑ ፣ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ከኡጋንዳ በመቀጠል ሁለተኛዋ አገር መሆኗንም ድርጅቱ ገልጿል።