ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለስ ተግባር በሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጀመራል- ብሪታኒያ
በብሪታኒያ 44 ሺ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞቸ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ
ጥገኘነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ ተግባር በርካታ ህጋዊ ማኖቆዎች ሊገጥሙት እንደሚችሉ እየተገለጸ ነው
ብሪታኒያ የመጀመሪያዎቹን ጥገኝነት ጠያቂዎች በሁለት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሩዋንዳ እንደምትመልስ አስታወቀች፡፡
ሩዋንዳ፤ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እና ስደተኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል የሚልየን ዶላሮች ስምምነት ባለፈው ወር ከብሪታኒያ ጋር መፈራረሟ የሚታወስ ነው፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ብሪታኒያ፤ ከጥገኝነት ጠያቂዎቹ የመጀመሪያዎቹን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሩዋንዳ እንደምትልክ አስታውቃለች፡፡
ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመመለሱ ተግባር ከመጪው ወርሃ ሰኔ 14 ቀን 2022 ጀምሮ መከናወን እንደሚጀምርም ነው የሀገሪቱ ባለስልጣናት ያስታወቁት፡፡
በመጀመርያው ዙር የሚመለሱት ጥገኝነት ጠያቂዎች ምን ያክል ናቸው ስለሚለው ግን በይፋ የተባለ ነገር የለም፡፡
የብሪታኒያ ባለስልጣናት ይህን ይበሉ እንጂ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በርካታ ከህግ ጋር የተገናኙ ማኖቆዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ እየተገለጸ ነው፡፡
ይህ አከራካሪ ሆኖ እየቀጠለ ያለ ጉዳይ ‘የፈጣሪን ስራ የሚጻረር’ ተግባር መሆኑ ከሃይማኖት መሪዎች ጀምሮ እስከ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲተቹት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ በመጠለያዎች ውስጥ ከነበሩ ስደተኞች ጥቂት የማይባሉ እየጠፉ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡
የመብት ተሟጋቾች የብሪታኒያ መንግስት ስደተኞችን የመንከባከብ ግዴታውን ለመሸሽ ያደረገው ነው በሚል መንቀፋቸውም አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጅ የብሪታኒያ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል ከሩዋንዳ ጋር የተደረሰው ስምምነት “ህገ ወጥ ስደትን ለማስቀረት የሚያግዝ ቁልፍ ስትራቴጂ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ ከ4 ሺ 850 በላይ ስደተኞች ወደ እንግሊዝ የገቡ ሲሆን ቁጥሩ ባለፈው ዓመት ከነበረው 831 የስደተኞች ቁጥር በእጅጉ የላቀ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ወደ ስልጣን ሲመጡ የህገ ወጥ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ ቃል በመግባት ነበር፡፡ ሆኖም ቁጥሩ በገቡት ቃል ልክ ከመቀነስ ይልቅ ስለመጨመሩ ይነገራል፡፡
የሩዋንዳው ስምምነት ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ጫና ለመቅለል በማሰብ የተደረገ እንደሆነም ነው የሚነገረው፡፡
በብሪታኒያ 44 ሺ ጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞቸ እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡