ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ተቀዳሚ የጉብኝታቸው አጀንዳ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል
የግብጹ ፕሬዝዳንት ፊልድ ማርሻል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ነገ ሱዳንን ይጎበኛሉ፡፡
የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በሁለትዮሽ እና በሌሎች ወቅታዊ ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርየም አል ሳዲቅ አል ማህዲ አስታውቀዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ቀዳሚ የጉብኝታቸው አጀንዳ ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ጉብኝቱ ሁለቱ ሃገራት ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በተስማሙ ሰሞን የተደረገ ነው፡፡
የሃገራቱ የጦር አመራሮች ከሰሞኑ (ባሳለፍነው ማክሰኞ) በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር የትብብር ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
መርየም አል ሳዲቅም በዚሁ ዕለት ከግብጹ አቻቸው ሳሚ ሹክሪ እና ከግብጽ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል መሃመድ ፋሪድ ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡
በተመራጩ የኡጋንዳ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በዓለ ሲመት ላይ ለመገኘት ወደ ካምፓላ አቅንተው የነበሩት የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን በጎረቤት ሃገር ደቡብ ሱዳን የአንድ ቀን ጉብኝት አድርገው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ከድንበር ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በመወዛገብ ላይ ትገኛለች፡፡ የእኔ ናቸው ወደምትላቸው የኢትዮጵያ ግዛታዊ አካባቢዎች ጦሯን ማዝመቷም ይታወቃል፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ጉዳዩ ከአሁን ቀደም በተደረገው ስምምነት መሰረት በሰላማዊ መንገድ በድንበር ኮሚቴው በኩል እንዲፈታና የሱዳን ጦር አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ ደጋግማ ብታሳስብም፡፡