የኮንጎ ፕሬዝደንት መልዕክተኞች በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ
ግብፅም የሱዳንን አቋም የደገፈች ሲሆን ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ተክጃለሁ የምትለው ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ውጭ አደራዳሪ አልሻም ብላለች
ሱዳን ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ 3 ዓለም አቀፍ ኃይሎች ድርድሩን እንዲመሩ አቋም መያዟን ለመልዕክተኞቹ ገልጻለች
በዲአር ኮንጎ ፕሬዝደንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ወደ ካርቱም የተላከ የኮንጎ የባለሙያዎች ቡድን ፣ በቀጣይ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር መክሯል፡፡
የቡድኑ አባላት ፣ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሦስቱን ሀገራት ሊያስማማ የሚችል የድርድር አቅጣጫን በተመለከተ ፣ ከዲአር ኮንጎ ፕሬዝደንት የተላከ መልዕክት ለሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት መሪ ሌ/ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን አድርሰዋል፡፡
ሁለቱ አካላት በነበራቸው ውይይት ወቅት ፣ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት የኮንጎው ፕሬዝዳንት የጀመሩትን ጥረት ያደነቁት አል-ቡርሃን ፣ ሱዳን ጥረታቸውን እንደምትደግፍ መግለጻቸውን ሱና ዘግቧል፡፡
የሱዳን የመስኖ እና የውሃ ሚኒስትር ያሰር አባስም ከቡድኑ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት ሱዳን ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ አሜሪካ ፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአውሮፓ ሕብረትም የአደራዳሪነት ሚና እንዲኖራቸው አቋም መያዟን ፣ ሚስተር አባስ ለወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የኮንጎው ፕሬዝደንት ሼሲኬዲ መልዕክተኞች አብራርተዋል፡፡ ችግሩ አፋጣኝ እልባት አግኝቶ ግድቡ የትብብር በር ከፋች እንዲሆን ሱዳን ምኞቷ እንደሆነም ነው ሚስተር አባስ የተናገሩት፡፡
በኮንጎ ፕሬዝደንት የተሰየመው የባለሙያዎች ቡድን አባላት ፣ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ግብፅ አቅንተው ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋርም ውይይት ያደረጉ ሲሆን ግብፅ ፣ አራት ዓለማቀፍ ኃይሎች ድርድሩን እንዲመሩ በሱዳን የቀረበውን ሀሳብ እንደምትደግፍ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ ለመልዕክተኞቹ ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን ግብፅ እና ሱዳን ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች እንዲገቡ ቢፈልጉም ፣ በግድቡ ጉዳይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ አደራዳሪ እንደማትሻ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በድርድሩ ላይ በታዛቢነት ከመሳተፍ ጀምሮ ሳይጠበቅ አደራዳሪ በመሆን የስምምነት ሰነድ እስከማዘጋጀት የደረሰችው አሜሪካ ለግብፅ እያዳላች እንደሆነ በመግለጽ ፣ ኢትዮጵያ “ስምምነቱን አልፈርምም” በማለት ራሷን ማግለሏ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ የትራምፕ አስተዳደር ፣ ኢትዮጵያ ያለስምምነት የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት በማከናወኗ ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረ ከፍተኛ የድጋፍ በጀት ቀንሷል፡፡ ይሁንና የጆ ባይደን አስተዳደር በግድቡ ድርድር ላይ አሜሪካ የምትከተለውን ፖሊሲ እንደሚፈትሽ አስታውቆ የድጎማ ቅነሳው ከግድቡ ጉዳይ ጋር መያያዙን እንደሚያቆም ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡