ሱዳን እና ግብፅ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በካይሮ ተገናኝተው በሕዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ያላቸውን አቋም ገልጸዋል
ግብፅ በሁሉም ወታደራዊ መስኮች የሱዳን ጥያቄዎችን ለማሟላት ዝግጁ መሆኗን አስታውቃለች
ሁለቱ ሀገራት በግብፅ ዋና ከተማ ካርቱም የተካሔደው የግብፅና የሱዳን የጋራ ወታደራዊ ኮሚቴ ሰባተኛ ዙር ስብሰባ ማጠናቀቂያ ላይ ነው ስምምነቱን የተፈራረሙት፡፡
በብዙዎ ዘንድ “ለኢትዮጵያ ማስጠንቀቂያ እንደመስጠት እና እንደማስፈራሪያ” የተወሰደውን ይህን ስምምነት የሁለቱ ሀገራት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሞች ናቸው የተፈራረሙት፡፡
ላለፉት ወራት የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን በማድረግ እና በከፍተኛ የወታደራዊ ባለስልጣኖቻቸው አማካኝነት አንዳቸው ወደ ሌላኛቸው ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን በማድረግ ከፍተኛ ወታደራዊ ግንኙነት ያደረጉ ሲሆን የዛሬው የስምምነት ፊርማም የዚህ ማሳረጊያ ነው፡፡
የግብፅ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናንት ጄኔራል መሐመድ ፋሪድ ስምምነቱን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ከሱዳን ጋር ያለው የወታደራዊ ትብብር ደረጃ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሀገራቸው የሱዳን ጥያቄዎችን በሁሉም ወታደራዊ መስኮች ለማሟላት ዝግጁ መሆኗንም በአፅንዖት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ያስቀመጡት “ሁለቱም ሀገራት የጋራ ፈተናዎች አሉባቸው” የሚል ነው፡፡ “ማንኛውም ድንገተኛ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የተስማማነውን ተግባራዊ ለማድረግ ፣ ዝግጁ ሀብት ፣ ጠንካራ ፍላጎት እና ውሳኔ አለን” በማለት በግልጽ ቋንቋ ሱዳን ወታደራዊ ድጋፍ ከጠየቀች በማንኛውም ጊዜ ለመድረስ ግብፅ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
የሱዳኑ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተናንት ጄኔራል መሐመድ ኦስማን አል ሁሴን በበኩላቸው “አሁን ያሉብንን ፈተናዎች ለመወጣት ለሚሰጡን ጠንካራ ድጋፍ የግብጽ ሠራዊት አባላትን እናመሰግናለን” ብለዋል፡፡ “ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ዛሬ ሰምምነቱ በተፈረመበት ወቅት አዲሷ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪያም አል-ማህዲ ካይሮ ተገኝተው ከግብፁ አቻቸው ሳሚ ሹክሪ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሁለቱ አካላት ከውይይታቸው በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫ ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር መጓተት ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ በቀጣይነት በሚኖረው ድርድር ላይ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ ፣ የተባበሩት መንግስታት ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረትም በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ የጋራ አቋም መያዛቸውንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ ሌላ አደራዳሪ እንደማትሻ በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በሦስቱ ሀገራት መካከል ካለው ከፍተኛ አለመግባባት በተጨማሪ ፣ ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ደግሞ ከሱዳን ጋር ውጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡