የሕዳሴውን ግድብ ድርድር ዓለማቀፋዊ ለማድረግ በሱዳን የቀረበውን ሀሳብ እንደምትደግፍ ግብፅ ገለጸች
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ አደራዳሪ እንደማትፈልግ ውጭ ጉዳይ አስታውቋል
ሱዳንና ግብፅ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ ተመድ ፣ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ይፈልጋሉ
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድርድር ዓለም አቀፍ ገጽታ እንዲላበስ በሱዳን የቀረበውን ሀሳብ ግብፅ እንደምትደግፍ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሹክሪ ትናንት ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ፣ አሜሪካ ፣ የተባበሩት መንግስታት እና የአውሮፓ ሕብረት የተካተቱበት ዓለም አቀፍ ቡድን ሦስቱን ሀገራት እንዲያደራድር በካርቱም የቀረበውን ሀሳብ ካይሮ እንደምትደግፍ ነው ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ የተናገሩት፡፡
ሚስተር ሹክሪ የግብፅን አቋም የገለጹት የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ከሆነችው ከዲአር ኮንጎ የጉዳዩ አስተባባሪ አልፎንሴ ንቱምባ ሉአባ ጋር በካይሮ በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
ምንም እንኳን ግብፅ እና ሱዳን ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎችን ቢጋብዙም ፣ በግድቡ ጉዳይ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ውጭ አደራዳሪ እንደማትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “ሌላ አሸናጋይ አንፈልግም ፤ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካውያን እንዲፈታ በሚለው መርህ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመሆኗ ጉዳዩ በሷ ብቻ እንዲታይ እንሻለን” ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በታዛቢነት ጀምራ ወደ አደራዳሪነት በመሸጋገር ፣ ከዚያም የስምምነት ሰነድ እስከማዘጋጀት የደረሰችው አሜሪካ ለግብፅ እያዳላች እንደሆነ በመግለጽ ኢትዮጵያ “ስምምነቱን አልፈርምም” በማለት ራሷን ማግለሏ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ የትራምፕ አስተዳደር ፣ ኢትዮጵያ ያለስምምነት የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት በማከናወኗ ለኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረ ከፍተኛ የድጋፍ በጀት ቀንሷል፡፡
አዲሱ የጆ ባይደን አስተዳደር ግን በግድቡ ድርድር ላይ አሜሪካ የምትከተለውን ፖሊሲ እንደሚፈትሽ አስታውቆ የድጎማ ቅነሳው ከግድቡ ጉዳይ ጋር መያያዙን እንደሚያቆም ይፋ አድርጓል፡፡
ሱዳን እና ግብፅ በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ላይ ሕጋዊ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ የመግባቢያ እንጂ አስገዳጅ ስምምነት ላይ የመድረስ ፍላጎት የላትም፡፡
በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር በወቅቱ የሕብረቱ ሊቀመንበር ዲአር ኮንጎ መሪነት እንደሚቀጥል በሚጠበቅበት ወቅት ነው ሱዳን እና ግብፅ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ያቀዱት፡፡ የግብፅን እና የሱዳንን እቅድ በተመለከተ እስካሁን ከተመድ ፣ ከዋሺንግተን እና ከብራሰልስ የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡