ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንዳያካሂዱ መከልከላቸውን አወገዘ
ቦርዱ በአዲስ አበባ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤያቸውን እንዳያካሂዱ በጸጥታ ሀይሎች መከልከላቸውን ገልጿል
ምርጫ ቦርድ ፍትህ ሚንስቴር ጉዳዩን እንዲመረምር እና በአጥፊዎች ላይ ክስ እንዲመሰርት ጥያቄ አቅርቤያለሁ ብሏል
ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ እንዳያካሂዱ መከልከላቸውን አወገዘ።
ምርጫ ቦርድ ባወጣው ሙግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባልተለመደ ሁኔታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የተከራዩዋቸውን አዳራሾች መከልከል እንዲሁም ጠቅላላ ጉባኤ ከማድረጋቸው በፊትና በኋላ በእስር፣ እንግልት፣ የማዋከብ ተግባራት እየተፈጸመባቸው ነው ብሏል ።
እናት ፓርቲ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ እና ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ (ጎጎት) ስብሰባ እንዳያካሂዱ መከልከላቸውን አረጋግጫለሁም ብሏል።
የእናት ፓርቲ የካቲት 26 ቀን ዓም በስላሴ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ ሊያደርገው ነበረው ስብሰባ ለጊዜው ስሙን ለይተን በላረጋገጥነው የህግ አስፈፃሚ ሀላፊ ትእዛዝ እነዳይካሄድ እንደተደናቀፈ ገልጿል።
እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ጋምቤላ ሆቴል ሊካሄድ የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ የሆቴሉ ባለቤቶች/አስተዳዳሪዎች፥ ስማቸው ተለየቶ ባልታወቀው የህግ አስፈፃሚ አባላት በደረሰባቸው ማስፈራሪያ ከመካሄድ እንደተሰናከለም ቦርዱ በመግለጫው ጠቁሟል።
የጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትህ ፓርቲ አስተባባሪዎች የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ተካፍለው በማግስቱ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም የፓርቲውን የጠቅላላ ጉባኤ ሰነዶች እንደያዙ በፌዴራል ፖሊስ ታስረው በማግስቱ ወደ ደቡብ ክልል ፖሊስ ተላልፈው እንደተሰጡ ቦርዱ መረዳቱንም አክሏል።
በዚሁም መሠረት ፓርቲዎች ጉባኤዎቻቸውን እንዳያደርጉ ያደረጉትም የጀመሩትን ጉባኤ ዳር እንዳያደርሱ የሚደረግባቸው ወከባ እንግልት እና እስር በፍፁም በቦርዱ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል።
እንዲሁም ድርጊቱ ቦርዱ በህግ የተሰጠውን ሃላፊነት እንዳይወጣ እና መሰረታዊ ሥራውን እንዳያከናውን ጫና ይፈጥራልም ብሏል፡፡
ጥፋቱ በየትኛውም አካል ቢፈጸም በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው ድርጊት አይደለም የሚለው ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ማከናወን መሰረታዊ ከሚባሉ የፓርቲ እንቅስቃሴዎች አንዱ ሲሆን ይህ ሁኔታ ከቀጠለ ፓርቲዎች መሰረታዊ ተግባራቸውን ማከናወን አለመቻላቸው ቦርዱ የተቋቋመበትን መሰረታዊ ስራ እንዳይሰራ የሚያደርግ፣ ህገመንግስታዊ የመደራጀት መብትን የሚጥስ እንደሆነም አስታውቋል።
ድርጊቱ በመድብለ ፓርቲ ስርአት የማሳደግ የሙከራ ሂደት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያስከትል ነውም ብሏል፡፡
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን መተላለፎች የፈፀሙ የህግ አስፈፃሚ አባላት በምርጫ አዋጁ የተጣለባቸውን የቦርዱን ሀላፊነቶች ለማስፈፀም የመተባበር ግዴታ ያለመወጣታቸውን ያሳያል ሲል ጠቁማል።
ድርጊቱ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በአንቀፅ 490 ህጋዊ ስበሳባዎችን ስለመከልከል እና ስለማወክ እንዲሁም በአንቀፅ 438 ህጋዊ የመንግስት ተቋም ስራ ስለማሰናከል እና የመተባበር ግዴታን ስላለመወጣት የተደነገገውን በመተላለፍ በወንጀል የሚያስጠይቃቸው እንደሆነ ቦርዱ በመግለጫው አስታውቋል።
በመሆኑ የፍትህ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የወንጀል ምርመራ መርቶ አጥፊዎቹ ላይ ክስ እንዲያቀርብ፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እና የተለያዩ ፀጥታ ኃይሎች በፓርቲዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያስቆሙ ጠይቋል።
የደቡብ ክልል ፖሊስ የጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ አስተባባሪዎች የሆኑትን አቶ ዮናታን፣ ሰለሞን እና አቶ ረመዳን ሙልጌታን በአስቸኳይ እንዲፈታም ቦርዱ ጠይቋል።
በመንግስት ስር የሚተዳደሩ የስብሰባ ቦታዎች እና አዳራሾች ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጠቅላላ ጉባኤዎች ክፍት እንዲሆኑ ይህም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እና በክልል ፐሬዜዳንቶች ጽህፈት ቤት አማካይነት እንዲፈፀም ቦርዱ መወሰኑን አስታውቋል።