ምርጫ ቦርድ ከመንግስት ያገኘውን ገንዘብ ለፖለቲካ ፓርቲዎች አከፋፈለ
በምርጫው የማይወዳደሩና እጩ ያላቀረቡ 5 ፓርቲዎች ደግሞ ባላቸው እውቅና እኩል ክፍያን አግኝተዋል
ክፍፍሉ በህጋዊነት ተመዝግበው ለሚንቀሳቀሱ 51 ፖለቲካ ፓርቲዎች የተደረገ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብ ክፍፍል አደረገ፡፡
ቦርዱ የገንዘብ ክፍፍል ያደረገው በህጋዊነት ተመዝግበው ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነው፡፡
በዚህም የቦርዱን እውቅና አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ 51 ፓርቲዎች በድምሩ 98 ሚሊዮን 624 ሺ 174 ብር ከ72 ሳንቲም ተከፋፍለዋል፡፡
ክፍፍሉ ቦርዱ ከአሁን ቀደም ያወጣውን ማከፋፈያ መስፈርት አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመካከረ በኋላ ባስቀመጠው ውሳኔ መሰረት የተፈጸመ ነው፡፡
የመጀመሪያው ዙር ክፍፍልም ተጠናቋል፡፡
እኩል እውቅናን፣ የቀረቡ እጩዎችን፣ ሴት እጩዎችን፣ አካል ጉዳተኛ እጩዎችን እና ሴት የስራ አስፈጻሚዎች ብዛትን ታሳቢ አድርጎ መፈጸሙንም ቦርዱ በይፋዊ የማህበረሰብ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ አስታውቋል፡፡
ክፍፍሉ የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነ ምግባር አዋጅ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችንም ታሳቢ አድርጓል፡፡
የፓርቲዎቹ የሂሳብ መዝገብ ችግር እንደሌለበት ተመርምሮ ሲረጋገጥ የሚፈጸምም ነው፡፡
በዚህም መሰረት መስፈርቶቹን በተሻለ አሟልተው የተገኙት መሪው ብልጽግና ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣እናት ፓርቲ እና ኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኅብር ኢትዮጵያ/ በክፍፍሉ የተሻለ የገንዘብ ድጋፍ ድርሻን አግኝተዋል፡፡
በምርጫው ባይወዳደሩና እጩ ባያቀርቡም እንኳ ባላቸው እውቅና እኩል ክፍያ ያገኙ ፓርቲዎችም አሉ፡፡
ለዚህም የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)ን ጨምሮ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት (ዓረና) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡