ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ውሳኔ ማድረጊያ ጊዜ የመወሰን ስልጣን የለውም ሲል ተቃወመ
ቦርዱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 12ኛው ክልል በህዝበ ውሳኔ እንዲመሰረት ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲላክለትም ጠይቋል
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ምርጫ ቦርድ በሶስት ወራት ህዝበ ውሳኔውን እንዲያካሂድ መወሰኑ ይታወሳል
ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ውሳኔ ማድረጊያ ጊዜ የመወሰን ስልጣን የለውም ሲል ተቃውሞውን ለፌዴሬሽን ም/ቤት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
ቦርዱ የፌዴሬሽን ም/ቤት በደቡብ ክልል ስር የሚገኙ 6 ዞኖች 5 ልዩ ወረዳዎች አንድ የጋራ ክልል ለመመስረት ወስነው ጥያቄ ስላቀረቡ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ውጤቱን ለም/ቤቱ እንዲያቀርብ ለቦርዱ ማሳወቁን ገልጿል።
ምክርቤቱ አንድ የጋራ ክልል እንዲመሰርቱ የወሰነላቸው ስድስት ዞኖች ማለትም የጋሞ፣ ወላይታ፣ ጎፋ፣ ጌዴኦ፣ ኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም 5 ልዩ ወረዳዎች ማለትም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ም/ቤቶችን ናቸው፡፡
ቦርዱ ይህን ሕዝበ ውሳኔ ለማደራጀት እንደ ግብአት ሆኖ ለቦርዱ ያገለግል ዘንድ ከላይ የተገለጹት የ6ቱ ዞኖች እና የ5ቱ ልዩ ወረዳዎች በየራሳቸው ም/ቤቶች ሕዝበ ውሳኔውን በጉዳዩ ላይ የሰጧቸውን ውሳኔዎች፣ ውሳኔያቸውን ለማስፈጸም ለፌዴሬሽን ም/ቤት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች፣ እንዲሁም አያይዘው ለም/ቤቱ የላኳቸው ሌሎች ሰነዶች እንዲላክለት ጠይቋል።
በሌላ በኩል የፌዴሬሽን ም/ቤት ከላይ በተጠቀሱት 6 ዞኖች እና 5 ወረዳዎች የሚደረገው የህዝብ ውሳኔ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲደራጅ ለቦርዱ ቀን ሙቁረጡ አግባብነት የለውም ብሏል።
በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 መሠረት በገለልተኛነት ከማንኛውም ተጽእኖ ነፃ የሆነ እውነተኛ ምርጫን ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በብቸኛነት የተቋቋመ ሕገ መንግስታዊ ተቋም መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።
ቦርዱ የተቋቋመበትን አላማ ለማስፈጸም የሚኖረውን የውሳኔ እና የአሰራር ነጻነት ምክርቤቱ ሊያከብር ይገባል ያለው ቦርዱ የህዝበ ውሳኔዎች ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ ለማካሔድ የሚወስደውን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ የመወሰን ስልጣኑ የቦርዱ መሆኑን አስታውቋል።
በህጉ መሰረት በአጠቃላይ ሁኔታ ከተቀመጡት የጊዜ ገደቦች ሳይወጣ የሚካሄዱበትን መርኃ ግብር ሰሌዳ የማዘጋጀት፣ የማጽደቅና እንደ አስፈላጊነቱም የማሻሻልና የማስፈጸም ሥልጣን የተቋሙ ብቻ መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ለቅድመ ዝግጅት የሚወስደውን ጊዜ ታሳቢ ያደረገ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ለምክር ቤቱ አሳውቃለሁ ብሏል፡፡