ምርጫ ቦርድ የ12ኛው ክልል ህዝበ ውሳኔ የድምፅ መስጫ ቀንን አሳወቀ
የፌዴሬሽን ም/ቤት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ወረዳዎች ላይ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል
ቦርዱ የድምፅ መስጫ ቀን ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲሆን ወስኗል
የኢትዮጵያ ብሄራ ምርጫ ቦርድ የ12ኛው ክልል ህዝበ ውሳኔ መስጫ ቀንን አሳወቀ።
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለተነሳው የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በሚል ሊካሄድ በታሰበው የህዝበ ውሳኔ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት እያደረገ ይገኛል።
- በኢትዮጵያ 12ኛ ክልል እንዲቋቋም የሚያስችል ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የፌዴሬሽን ም/ቤት ወሰነ
- ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ውሳኔ ማድረጊያ ጊዜ የመወሰን ስልጣን የለውም ሲል ተቃወመ
በዚህ ውይይት ላይ ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቦርዱ ህዝበ ውሳኔ እንዲያካሂድ የወሰነውን ውሳኔ ማስፈጸም የሚችልበትን እቅድ ይፋ አድርጓል።
በቦርዱ እቅድ መሰረት በደቡብ ክልል ስር ባሉት ስድስት ዞኖች እና አምስት ወረዳዎች ላይ የህዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጫ ቀን ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚሆን አስታውቋል።
የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች፣ እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ደግሞ ህዝበ ውሳኔው የሚካሄድባቸው ቦታዎች ናቸው።
ቦርዱ በህዝበ ውሳኔው 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ ድምጽ እንደሚሰጡም አስታውቋል።
አርባ ምንጭ የህዝበ ውሳኔው ማስተባበሪያ ምዕከል ይሆናል የተባለ ሲሆን የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ውጤት የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ይደረጋል።
የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖችና የም ልዩ ወረዳ በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንድ ላይ እንደሚቀጥሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፍነው ነሀሴ መወሰኑ ይታወሳል።
በውይይት መድረኩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በቦርዱ ጊዜያዊ የህዝበ ውሳኔ ድምፅ መስጫ ቀን ላይ አስተያየታቸው ሰጥተዋል።
የጉራጌ ዞን ከሀዲያ፤ ከስልጤ፣ ከከንባታ ጠንባሮና ከየም ልዩ ወረዳ ጋር በክላስተር ተደራጅቶ ክልል እንዲሆን የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።