ምርጫ ቦርድ የሶማሌ ክልል ላቀረበው ቅሬታ ምላሽ ሰጠ
ምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል ባቀረበው አቤቱታ መሰረት በ 8 ቀበሌዎች ምርጫ ጣቢያ እንዳይቋቋም ወስኖ ነበር
ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምጻቸውን የሚሰጡበት ስፍራ ከመሆን ባለፈ የአስተዳደር ወሰኖች ክርክር የመወሰን ውጤት አይኖራቸውም ብሏል
የሶማሌ ክልል፤ ቀደም ሲል የነበሩት አምስት ሀገራዊ ምርጫዎች ሲደረጉ በነበረው አግባብ የምርጫ ጣቢያዎችን የማይቋቋሙ ከሆነ “በምርጫው ለመሳተፍ እቸገራለሁ” በሚል ላቀረበው ቅሬታ ምርጫ ቦርድ ምላሽ ሰጠ፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በ 8 ቀበሌዎች ላይ ያቀረበውን አቤቱታ መነሻ አድርጎ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀበሌዎቹ ሊከፈቱ የነበሩ 30 የምርጫ ጣቢያዎች በአካባቢው እንዳይቋቋሙ መወሰኑን ተከትሎ ነበር፤ የሶማሌ ክልል በርዕሰ መስተዳድሩ የተፈረመ ደብዳቤ ትናንት ለቦርዱ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡
የሱማሌ ክልል “ቦርዱ የክልሉን አስተያየት ሳይጠይቅና በደብዳቤ የተገለጸውን ጉዳይ ወደ ጎን ብሎታል” ብሎ የነበረ ቢሆንም ቦርዱ ግን ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት በፌዴራሉ የምርጫ ደህንነት ታስክ ፎርስ ከታቀፉት የፌደራል የሕግ አስፈፃሚ አካላት ዕገዛ እና ምክረ ሀሳብ ጠይቆ እንደነበር ገልጿል፡፡
ቦርዱ፤ የሰጠው ውሳኔ ” የአፋር ክልልን ወይም የሶማሌ ክልልን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄ በማጽደቅ ወይም ውድቅ በማድረግ የተሰጠ ውሳኔ እንዳልሆነ የሶማሌ ክልል ሊገነዘብ ይገባል” ሲል ገልጿል፡፡ ቦርዱ፤ የምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምጻቸውን የሚሰጡበት ስፍራ ከመሆን ባለፈ የአስተዳደር ወሰኖች ክርክር የመወሰን ውጤት እንደማይኖራቸው ገልጾ፤ የአስተዳደር ወሰኖችን የመከለል ምንም አይነት ሥልጣን እንደሌለውም አስታውቋል፡፡
ምርጫ ጣቢያዎችን የት እና እንዴት እንደሚቋቋሙ መወሰን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኣዋጅ የተሰጠ ኃላፊነት እንደሆነ ያነሳው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ የሚያከናውናቸው ተግባራት በመሆናቸው “የርዕሰ መስተዳድሮች የስልጣን ውዝግብ ምክንያት ሊሆን አይገባም” ብሏል፡፡
የምርጫ ተወዳዳሪዎች ”ፓርቲዎች እና እጨዎቻቸው እንጅ ክልላዊ መንግስታት እንዳልሆኑ እየታወቀ የሶማሌ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ‘በምርጫው ለመሳተፍ እንቸገራለን’ ሲሉ የገለፁት በህግ እይታ ምንም ትርጉም የማይሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል” ሲል ቦርዱ አስታውቋል፡፡