በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከ134 ሺህ በላይ ታዛቢዎች እንደሚሳተፉ ቦርዱ ገለፀ
8 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 61 ሺህ 851 ሴት ታዛቢዎችን አቅርበዋል
ምርጫውን ለመታዘብ ካመለከቱ 111 ድርጅቶች መካከል 36ቱ ተመርጠዋል
በዘንድሮው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከ134 ሺህ በላይ ታዛቢዎች እንደሚሳተፉ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለመታዘብ ፍላጎት ላላቸው የሀገር ዉስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፍቃድ ለማግኘት ማመልከቻዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት 111 ድርጅቶች እውቅናን ለማግኘት አመልክተዋል ብሏል።
ድርጅቶቹ ያቀረቡትን ማመልከቻዎች እና ተያያዥ ሰነዶች በምርጫ ህጉ፣ በወጣው ጥሪ እና በመመሪያዉ የተደነገጉትን መስፈርቶች እና ግዴታዎች ማሟላታቸውን ካረጋገጠ በኋላ 36ቱ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ እንዲታዘቡ መመረጣቸውን ቦርዱ ገልጿል፡፡
የተመረጡት 36ቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 134 ሺህ 109 ታዛቢዎችን ማቅረባቸውንም ቦርዱ አሳውቋል።
ከታዛቢዎች መካከልም በሴቶች ጉዳይ ላይ 8 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 61 ሺህ 851 ሴት ታዛቢዎችን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ስር የታቀፉ 7 ማህበራት ደግሞ 244 ታዛቢዎችን አቅርበዋል ተብሏል።
በሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ሂደትን ለመታዘብ የተመረጠ 1 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ደግሞ 100 ታዛቢዎችን ሲያቀርብ በስሩ 37 ያህል ሲቪል ማህበራትን ያቀፈ የሲቪል ማህበረሰብ ኔትወርክ ይገኝበታል።
ቦርዱ በቀጣይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተመረጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እንደሚያዘጋጅም ገልጿል።