ውዝግብ በተነሳባቸው 8 ቀበሌዎች ሊከፈቱ የነበሩትን 30 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ ቦርዱ ውሳኔ አሳለፈ
በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች በአቅራቢያቸው ባለ ሌላ ቀበሌ መመዝገብ እና ድምጻቸውን መስጠት የሚችሉ መሆኑን አስታውቋል
የምርጫ ክልሎች የየትኛውም የመንግስት አስተዳድር መዋቅር አካላት አለመሆናቸውንም ቦርዱ አስታውቋል
ውዝግብ በተነሳባቸው 8 ቀበሌዎች ሊከፈቱ የነበሩትን 30 የምርጫ ጣቢያዎች እንዳይቋቋሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ አሳለፈ
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፣ የምርጫ ክልሎች አላግባብ በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ ቀበሌዎች ተጠርተዋል በሚል የካቲት 05 ቀን 2013 በተጻፈ ደብዳቤ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ እቅርቧል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የምርጫ ጣቢያዎች ያለአግባብ በሶማሌ ብሔራዊ ክልል መንግስት ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ስም ይፋ ተደርገዋል የሚል ያቀረበውን አቤቱታ በመመልከት ነው ውሳኔ ያሳለፈው።
ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎችን ሲያደራጅ በአቅራቢያው ያሉ ዜጎች በመራጭነት ለመመዝገብ እንዲሁም ድምጻቸውን እንዲሰጡ ለማስቻል በማሰብ ሲሆን የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀትም ባለፉት 5 አጠቃላይ ምርጫዎች ተመሳሳይ መስፈርቶችን በመጠቀም ሲከናወን የቆየ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ምርጫ ጣቢያዎች ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት የሚመቻቹ የመመዝገቢያ እና ድምጽ መስጫ ቦታዎች ሲሆኑ የየትኛውም የመንግስት አስተዳድር መዋቅር አካላት አለመሆናቸውንም አስታውቋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በሚያከናውናቸው የምርጫ ኦፕሬሽን ተግባራት በተለያዩ ደረጃዎች የራሱን መዋቅር የሚያዘጋጅ ሲሆን እነዚህ መዋቅሮች ከመንግሰት ቋሚ መዋቅር ጋር ተመሳሳይነት የላቸውም ብሏል።
ምንም አንኳን ከላይ እንደተጠቀሰው ቦርዱ በ2007 ዓ.ም የተጠቀመበትን የመረጃ ዝርዝር ለ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ቢጠቀምም፣ የምርጫ ጣቢያዎች የአስተዳደር ወሰኖችን የሚወስኑ መገለጫዎች ባይሆኑም ቦርዱ ምርጫ በምንም መልኩ የሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን በማሰብ
• በጋላእቶ/አዳይሌ
• በአዳይቱ/አዳይቱ
• በቴውኦ/አላሌ
• በጉርሙዳሊ/ዳንሌሄላይ
• በኡንዳፎኦ/ኡንዱፎ • በጋዳማይቱ/ጋርባኢሴ
• በአፍዓሶ/አፉአሴ
• በባላእቲ ጎና/መደኒ ቀበሌዎች ሊከፈቱ የነበሩትን 30 የምርጫ ጣቢያዎች በአካባቢው እንዳይቋቋሙ ወስኗል።
በዚህም መሰረት በአካባቢው የሚኖሩ እና የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ መስጠት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ዜጎች በአቅራቢያቸው ባለ ሌላ ቀበሌ መመዝገብ እና ድምጻቸውን መስጠት የሚችሉ መሆኑንም አስታውቋል።