“ከእነ አቶ ዳዉድ ኢብሳ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለንም“ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ከእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ቡድን
ምርጫ ቦርድ ኦነግን በሚመለከት ከእኛ ጋር ነው ግንኙነቱ አቶ በቴ ኡርጌሳ ከእነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ቡድን
ምርጫ ቦርድ በኦነግ አመራሮች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጊዜያዊ ጉባዔ እንዲቋቋም ቀደም ብሎ ወስኗል
ምርጫ ቦርድ በኦነግ አመራሮች መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ጊዜያዊ ጉባዔ እንዲቋቋም ቀደም ብሎ ወስኗል
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እርስ በእርስ ባለመግባባት በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ እና በእነ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመሩ የሚባሉ ቡድኖች መፈጠራቸው ይታወሳል፡፡
በሁለቱ ግለሰቦች የተጻፉ ደብዳቤዎችም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገቢ መሆናቸውን ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል፡፡
በጉዳዩ ላይ አል ዐይን አማርኛ ከኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቀጀላ መርዳሳ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ኃላፊው ሦስተኛ አካል ወደ አንድ ካላመጣ በስተቀር ከእነ አቶ ዳውድ ኢቢሳ ጋር መነጋገር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ሁለታችሁም ኦነግ እኛ ነን እያላችሁ ነው ማነው ኦነግ በሚል ለቀረበላች ጥያቄ “ ማዕከላዊ ኮሚቴው የተበታተነ ነው፣ ከሥራ አስፈጻሚ ግን ከአቶ ዳውድ በስተቀር ሁሉም ከእኛ ጋር ናቸው“ብለዋል፡፡
ከእነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ቡድን ጋር ያሉት አቶ በቴ ኡርጌሳ ከአል ዐይን ጋር በነበራቸው ቆይታ የእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ቡድን የብልጽግናን አላማ እያራመዱ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አል ዐይን የጠየቃቸው የእነ አቶ አራርሶ ቡድን አባል አቶ ቀጀላ መርዳሳ ይህ ተራ የሥም ማጥፋት ዘመቻ እንደሆነ ገልጸው“ ይህ የእነ አቶ ዳውድ የቆየ የፖለቲካ ሴራ ነው፤ከዚህ ቀደምም የሰው ስም ሲያጠለሹ ነበር፣ ስለዚህ ይህ ላለፉት 20 ዓመታት በላይ የተካኑበት በመሆኑ ጆሮ አንሰጠውም “ ሲሉ መልሰዋል፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ ከእርሳቸው በሃሳብ ያፈነገጡ ሰዎች ከፖለቲካ እንዲርቁ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ነው አቶ ቀጀላ የገለጹት፡፡ እናም ዛሬ እኛ ከእነ አቶ ዳውድ ጋር ስለተጣላን የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱብን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አቶ በቴ ኡርጌሳ እነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ከድርጅት ሥነምግባር ስላፈነገጡ እንዲወጡ ተደርጓል ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንኙነቱ ከእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ጋር ሳይሆን ከእኛ ጋር ነው ብለዋል፡፡ አቶ ቀጀላ ደግሞ እነ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከድርጅቱ ታግደዋል ያሉ ሲሆን አሁን ላይ ድርጅቱ በአቶ አራርሶ እየተመራ ነው ብለዋል፡፡
አቶ በቴ ግን አሁንም አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦነግ ሊቀ መንበር ናቸው ሲሉ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ምን እየተካሄደ እንደሆነ እንደማያውቁ የገለጹት አቶ በቴ አቶ ዳውድ አሁን በቤት ውስጥ ሲሆኑ ወደእርሳቸው ጋር መግባትም ሆነ መውጣ እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን አለመግባባት ለመፍታት በእነ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመረጥ አንድ በእነ አቶ አራርሶ የሚመረጥ አንድ እንዲሁም በባለጉዳዮቹ የሚመረጡትን ባለሙያዎች በሰብሳቢነት የሚመራ ሌላ አንድ ባለሙያ ቦርዱ መርጦ በመመደብ የባለሙያዎች ጊዜያዊ ጉባዔ እንዲቋቋም መወሰኑ ይታወሳል፡፡
በዚህም መሰረት በሁለቱ አካላት እና በቦርዱ የተመረጡ ባለሞያዎች ጉዳዮን አጣርተው በሚያቀርቡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑንም ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ገልጿል፡፡