አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ሊቀመንበርነት ለምን ታገዱ?
በፓርቲው የሚታየው የክፍፍል አዝማሚያ ዉስጣዊ ችግር መሆኑን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ተናግረዋል
የአቶ ዳውድ ጉዳይ በፓርቲው የዲሲፒሊን እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ እየታየ መሆኑ ተገልጿል
አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ሊቀመንበርነት ለምን ታገዱ?
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር የሆኑት ዳውድ ኢብሳን በጊዜያዊነት መታገዳቸውን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ለአል ዐይን ተናገሩ፡፡ አቶ ዳውድ የታገዱት የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ባደረገው ስብሰበ መሆኑን ነው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ቀጄላ የገለጹት፡፡
አቶ ዳውድ ኢብሳ በስራ አስፈጻሚው በጊዜያዊነት ሊታገዱ የቻሉት ለረዥም ጊዜ በስራ ገበታቸው ላይ መገኘት ባለመቻላቸው እንደሆነ አቶ ቀጄላ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከዲሲፒሊን ጋር በተያያዘም የሚነሳባቸው ጉዳይ እንዳለ ይፋ አድርገዋል፡፡ የስራ አስፈጻሚው ካደረገው ስብሰባ ጋር ተያይዞ ዉዥንብሮች መፈጠራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
አቶ ቀጄላ መርዳሳ
ከሳምንታት በፊት “የደህንነት ስጋት አለባቸው” በሚል አቶ ዳውድ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ተወስኖ ለ2 ሳምንታት ያህል ከቤታቸው እንዳይወጡ መደረጉ ይታወቃል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር በስራ ገበታቸው ላይ መገኘት ያልቻሉበት ምክንያት ከዚህ ጉዳይ ጋር ይያያዝ እንደሆነ አቶ ቀጄላን ጠይቀናቸዋል፡፡ ለጥያቄው በሰጡን ምላሽ መንግስት የጸጥታ ስጋት ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት ለእርሳቸው ጥበቃ በሚያደርግበት ወቅት የፓርቲው ጽ/ቤትም ጥበቃ እየተደረገለት ለ 2 ሳምንታት ያህል መቆየቱን አንስተዋል፡፡
መንግስት ደህንነትን ለማስጠበቅ በሚል የወሰደው እርምጃ እንዳለ ሆኖ ከዚያ በኋላ አቶ ዳውድ አንድ ጊዜ ቢሮ ቢገቡም የአመራር አባላትን ሰብስበው ማነጋገር ሲጠበቅባቸው ይህን አለማድረጋቸውን አቶ ቀጄላ አንስተዋል፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ወደ ስራ አለመመለሳቸውን የገለጹት አቶ ቀጄላ በስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙበትን ምክንያት እስኪያሳውቁ እና ዉዥንብሮች እስኪጣሩ በጊዜያዊነት እንዲታገዱ መወሰኑን ነው ያብራሩት፡፡
“ጉዳዩ ለዲሲፒሊን እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ ተመርቶ የማጣራት ስራ እየተከናወነ ነው” ያሉት አቶ ቀጄላ ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ አቶ ዳውድ ወደ ስራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የአቶ ዳውድ ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ በፓርቲው ህገ ደንብ እና የስራ ሥነ ምግባር መሰረት ምክትላቸው የእርሳቸውን ተግባራት እያከናወኑ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ከአቶ ዳውድ ጋር የተያያዘው ጉዳይ “የፓርቲው ዉስጣዊ ጉዳይ በመሆኑ በራሳችን አሰራር የምንፈታው ነው ፤ ጉዳዩ ተጣርቶ በአስቸኳይ እልባት ይሰጠዋል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በትናንትናው እለት አቶ ዳውድ ኢብሳ የፓርቲውን ም/ሊቀመንበር አራርሳ ቢቂላን እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊውን እራሳቸውን አቶ ቀጄላን ጨምሮ 6 ከፍተኛ አመራሮችን ከስራ አግደዋል በሚል የተሰራጨውን መረጃ በተመለከተ ሀሰት መሆኑን አቶ ቀጄላ ከአል ዐይን ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡
አቶ ቀጄላ እንዳሉት በእርሳቸው ፊርማ ታገዱ የተባለው ጉዳይ የተሳሳተ ነው፡፡ ተሰራጨ የተባለው መረጃ “በዉጭ ሀገር እና በሀገር ዉስጥ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች ባደረጉት ስብሰባ 6 ከፍተኛ አመራሮችን አገዱ” የሚል መሆኑን በማንሳት ይህን መረጃ ያሰራጩት 4 የፓርቲው የበታች አመራሮች ናቸው ብለዋል፡፡ ሲጀመር ፓርቲው በዉጭ ሀገር አመራር እንደሌለው የተናገሩት አቶ ቀጄላ ይህን የሀሰት መረጃ ያሰራጩ ግለሰቦች ጉዳይም በዲሲፒሊን እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴው እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡
በፓርቲው ያለውን የመከፋፈል አዝማሚያ በተመለከተ ጉዳዩ የዉስጥ ችግር እንጂ የማንም ዉጫዊ አካል እጅ የገባበት አለመሆኑን በማንሳት በፓርቲው ዉስጣዊ አሰራር እልባት ያገኛል ብለዋል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ቀጄላ መርዳሳ፡፡