በኦነግ አባላት አለመግባባት ዕልባት ለመስጠት የባለሙያዎች ጊዜያዊ ጉባዔ ሊቋቋም ነው
ለሁለት የተከፈሉት የኦነግ አመራር አባላት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የየራሳቸውን አቤቱታ አቅርበዋል
ምርጫ ቦርድ ጉባዔው በሚያቀርብለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ ገልጿል
በኦነግ አባላት አለመግባባት ዕልባት ለመስጠት የባለሙያዎች ጊዜያዊ ጉባዔ ሊቋቋም ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አመራር አባላት የአመራር ለውጥ እና እገዳን አስመልክቶ የተለያዩ አቤቱታዎች ሲደርሱት ነበር፡፡
በአንድ በኩል በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በቁጥር 06/ABO/12 እና 7/08/12 05/03/19 በቁጥር 08/ABO/12 በተፃፉ ሁለት ደብዳቤዎች የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በፓርቲው ሊቀመንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ ላይ የእግድ ውሣኔ አስተላልፏል ሲሉ ለቦርዱ በማሳወቅ ቦርዱ ውሳኔውን እንዲያጸድቅላቸው ጠይቀዋል፡፡
ቦርዱ እንደገለጸው በሌላ በኩል አቶ ዳውድ ኢብሣ በ08/10/2020 (እ.ኤ.አ) በቁጥር 0211/xly/abo/2020 በተፃፈ ደብዳቤ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በሆኑት አቶ አራርሶ ቢቂላ፣ አቶ ቶሌራ ተሾመ፣ አቶ አቶምሣ ኩምሣ እና የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የሆኑት አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶ አርብቾ ዲማ እስከሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ ስለተወሰነ ይኸው ውሳኔ በቦርዱ እውቅና እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንኑ በፓርቲው አባላት መካከል የተፈጠረውን ያለመግባባት የሚያስረዱትን ከዚህ በላይ የተገለፁትን ደብዳቤዎችና ሌሎች የጽሑፍ አቤቱታዎችን መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ መመርመሩን አስታውቋል፡፡ በፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባዔ የማቋቋም ሥልጣን አለው፡፡
በመሆኑም በእነ አቶ ዳውድ ኢብሣ የሚመረጥ/የምትመረጥ አንድ ፣ በእነ አቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመረጥ/የምትመረጥ ሌላ አንድ ፣ እንዲሁም እነዚህን ሁለት በባለጉዳዮቹ የሚመረጡትን ባለሙያዎች በሰብሳቢነት የሚመራ/የምትመራ ሌላ አንድ ባለሙያ ቦርዱ መርጦ በመመደብ የባለሙያዎች ጊዜያዊ ጉባዔ እንዲቋቋም መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ወስኗል፡፡ በዚህም መሰረት በሁለቱ አካላት እና በቦርዱ የተመረጡ ባለሞያዎች ጉዳዮን አጣርተው በሚያቀርቡት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተመስርቶ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
የኦነግ አመራር አባላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሁለት ተከፍለው አንዳቸው ሌላኛቸውን ህገወጥ እያሉ በመወነጃጀል የተለያዩ መግለጫዎችን በፓርቲው ስም እያወጡ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡