ግድቦች በቂ ውሃ በመያዛቸው ዘንድሮ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፈረቃ አይኖርም ተባለ
በኢትዮጵያ የሚገኙ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ከዚህ ቀደም ካሉት 5 አመታት ከነበራቸው አማካይ የውሃ መጠን ያልተናነሰ ውሃ በመያዛቸው ዘንድሮ በኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት የፈረቃ ስርዓት እንደማይኖር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሙዩኒክሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞገስ ሞኮንን መግለጻቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከሃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል ተከዜ፣ ቆቃ፣ ፊንጫ፣ መልከዋከና፣ ግልገል ጊቤና አመርቲ ነሺ የሚገኙበት ሲሆን ሁሉም ከአምስት አመታት በአማካይ ሲይዙት ከነበረው የውሃ መጠን ያልተናነሰና ከፍ ያለ ውሃ ይዘዋል ነው የተባለው፡፡
በሃገሪቱ በየአመቱ ከ9 እስከ 13 በመቶ እያደገ የሚሄድ የሃይል ፍላጎት ቢኖርም የተወሰኑ ግድቦች ከዚህ በፊት ከነበረው የውሃ መጠን የተሸለ ከፍታ በማሳየታቸው እጥረት አይከሰትም ብለዋል አቶ ሞገስ፡፡
ስለዚህ ዘንድሮ ግድቦቹ ለኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ የሚበቃ በቂ ውሃ በማከማቸታቸው ወደ ፈረቃ አይገባም ነው ያሉት፡፡
ግልገል ጊቤ 3 በየአመቱ በአማካይ 830 ሜትር ከፍታ ይገኝ ከነበረው በ2012 ዓ.ም 882 ሜትር ከፍታ ላይ ሲገኝ ስራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የዚህ አመት ከፍታ በትልቅነት የተመዘገበ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የኤሌትሪክ ሃይል ፍላጎትን ሙሉ በሙሉ ለማሟላት አዳዲስ ግድቦች እየተገነቡ ሲሆን 254 ሜጋ ዋት ሃይል ማመንጨት የሚችለው ገናሌ ዳዋ 3 የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ ተጠናቆ በሙከራና ፍተሻ ላይ ይገኛል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ግድቡ በሰዓት 1 ሺህ 640 ሜጋ ዋት በአመት የማመንጨት አቅም አለው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ተከስቶ በነበረው የግድቦች ውሃ መጠን መቀነስ ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወደ ፈረቃ መገባቱ የሚታወስ ነው፡፡
ምንጭ፡- ኢቢሲ