አዲስ የደህንነት ቀበቶ መመሪያ ከጥቅምት 18 ጀምሮ እየተተገበረ ይገኛል
አዲሱ የደህንነት ቀበቶ መመሪያ ከጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለአሽከርካሪውና ለሁሉም ተሳፋሪዎች
እየተተገበረ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተዉ፣ በብዙሃን ትራንስፖርት ቆመው የሚጓዙ እና አጭር ርቀት የሚጓዙ ቀበቶ እንዲያስሩ የሚያስገድደው ህግ አሁን በአዲሱ መመሪያ አስገዳጅነት አይኖረዉም፡፡
በመመሪያው መሰረት በመንግስትና በግል ለሰራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ እስከ 150 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ ሚኒባሶችና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ ከ5 እስከ 8 መቀመጫ ያላቸው ተሽከርካሪዎች፣ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ልዩ ባሶችና ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች የደህንነት ቀበቶ መግጠምና መጠቀም አለባቸው፡፡
ከዚህ ባለፈም የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ ከ12 እስከ 15 ሰው የሚጭኑና በከተማ ውስጥ
አገልግሎት የሚሰጡ፣ የብዙሃን አገልግሎት የሚሰጡ የከተማ አውቶብሶች ለአሽከርካሪውና ፊት ወንበር ላይ
ለሚቀመጡ ተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ መጠቀም ይኖርባቸዋል።
በተጨማሪም ለግል አገልግሎት የሚጠቀሙ አውቶሞቢሎች የህፃናት ደህንነት መጠበቂያ ቦርድ ያለው ማካተት
ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።
በአስመጪዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ አዲስ የመንግስት፣ የግል፣ የህዝብና የጭነት ተሽከርካሪዎች በባለስልጣን
መስሪያ ቤቱ በሚወጣው መስፈርት መሰረት ለአሽከርካሪውና ለተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ የተገጠመላቸው መሆን
ይጠበቅባቸዋል።
ከጥቅምት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የፀናው ይህ መመሪያ፣ በባለሁለትና በባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ በግዳጅ ስራ ላይ በተሰማሩ የፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ተሽከርካሪዎች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም።
ኢትዮጵያ በየአመቱ ከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ከሚያስተናግዱ ሀገራት መካከል የምትጠቀስ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቀነስ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ጠንከር ያለ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የትራፊክ አደጋ አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡