ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ሊገጥሟት የሚችሉ አራት ሴናሪዮዎች ይፋ ተደረጉ
"የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032" በሚል ርእስ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ህዳር 23/2012 አ.ም. በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ሀገር አቀፍ የውይይት መድረኩን ፎረም ኦፍ ፌዴሬሽን እና ዴስትኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ናቸው በጋራ ያዘጋጁት።
በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች ፣የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፣የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
መድረኩ የሀገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትን በማቀራረብ የወደፊት የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ ለመወያየት በማለም የተዘጋጀ ነው፡፡
የዴስቲኒ ኢትዮጵያ በአገሪቱ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶች፣ ክልሎች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና ምሑራን የተውጣጡ 50 ሰዎችን በመምረጥ ላለፉት ስድስት ወራት ዝግ ስብሰባዎችን በማካሄድ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት አገራችን ሊገጥሟት የሚችሉ አራቱን ሴናሪዎች መቅረፁን የዴስቲኒ ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ንጉሴ አክሊሉ ተናግረዋል ።
አራቱ ሴናሪዎች አፄ በጉልበቱ ፣ ሰባራ ወንበር ፣ የፋክክር ቤት እና ንጋት ናቸዉ ።
የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ እንዲህ አይነቱ መድረክ ሁላችንም ለኢትዮጵያ እንደምናስፈልጋት የሚያስተምር ነው ብለዋል።
ሂደቱ በአብሮነት እና በመቀራረብ ውስጥ ያለውን የልብ ጆሮ የመክፈት ሀይልን ያመላከተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሂደቱ አዲስ የፖለቲካ ባህልን ለመገንባት አስቻይ መንገድን ያሳየን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ራስን እንዴት ማሸነፍና መስራት ይቻላል የሚለውን እና ህግን ማክበር እንዴት እንደሚቻል ያስተማረ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።
የሴናሪዮ ምክክር ሂደት ውጤትም ለመንግስት ግብአት ሆኖ የሚያገለግል መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት የገለፁት።
ከአራቱ ሴናሪዮ (እጣ ፈንታዎች) ውስጥ “ንጋት” በሚል የተሰየመችውን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ዛሬ ላይ በጉልበት፣ በእውቀት እና በሀብት ሳንሰስት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
“በወገኖቼ ላይ ትልቅ እምነት አለኝ” ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት፥ “የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ሰላም የሚፀልይ፣ ዱአ የሚያደርግ እና የሚተጋ በመሆኑ እምነት አለኝ” ብለዋል።
በመድረኩ ላይ ከ50 በላይ የተቋማት መሪዎች በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ሲያደርጉት በነበረው ምክክር ዙሪያ ንግግር አድርገዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና ተወካዮቹ ከዚህ ቀደም በዚህ መድረክ ስር በጋራ በነበራቸው ቆይታ ስለ ሀገሪቱ ፖለቲካ በስፋት መምከራቸውን እና በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮች በውይይት ብቻ የሚፈቱ እንደሆኑ ከመግባባት መድረሳቸውን አስታውቅዋል።
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፥ መድረኩ በሀገር ጉዳይ ሁሉም በንግግር የሚፈታ መሆኑን ልምድ የተገኘበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአብን ሊቀ መንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፥ መድረኩ የተራራቀ አቋም ያላቸው የፖለቲካ ሀይሎችን ያቀራረበ መሆኑን ተናግረዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ምንም አይነት የተራራቀ የአቋም ልዩነት ቢኖርም፤ በመቀራረብ እና በመወያየት የማይፈታ ነገር እንደሌለ ያስተማረ መሆኑን ተቅሰዋል።
የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም፥ “መድረኩ መጀመሪያ ሲጀመር ውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ነበረኝ፤ ወደ ስራ ስንገባ ግን ቀስ በቀስ በመነጋገር፣ በመወያየትና በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ መፈለግ እንደሚቻል ልምድ ያገኘሁበት ነው” ብለዋል።
የአዴፓ ተወካይ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል፥ “በመድረኩ በጋራ በመሆን ሀገርን፣ የዴሞክራሲ ስርዓትን፣ መንግስትን እና ኢኮኖሚን መገንባት እንደሚቻል አረጋግጫለሁ” ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌ ተወካዮችም፥ መድረኩ ለኢትዮጵያ መፃኢ እድል በር የሚከፍት መሆኑን በመግለጽ፤ ለኢትዮጵያ ስንል ሁላችንም ዝቅ ብለን እንስራ ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የመድረኩ ተሳታፊዎች “ንጋት፣ የፉክክር ቤት፣ አፄ በጉልበቱ እና ሰባራ ወንበር” በሚሉ አራት ሴናሪዮዎች (እጣ ፈንታ) ዙሪያ ለስድስት ወራት በዝግ ስብሰባ በግልፅ በሀገሪቱ ፈታኝ እና ወሳኝ ሁኔታዎች ዙሪያ መወያየታቸውን አስታውቅዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በውይይታቸው የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን፥ ሁሉም ለኢትዮጵያ ሰላም በይቅርታ እና በወንድማማችነት መንፈስ በትጋት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ ፣ ሰላም ሚኒስቴር