የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውሃ የሚኒስትሮች የካይሮ ስብሰባ ተጠናቀቀ
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና አለቃቀቅ ጉዳይ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች በግብፅ ካይሮ ለ ሁለት ቀናት ያካሄዱት የቴክኒክ ስብሰባ ተጠናቀቀ።
የካይሮው ስብሰባ አገራቱ በአዲስ አበባ ባካሄዱት እና የጋራ መግባባት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ ነው የተካሄደው።
ሶስቱ ሀገራት በአሜሪካ ግብዣ ዋሺንግተን ዲሲ ላይ ከወር በፊት በነበራቸው ውይይት፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት በገቡት ቃል መሰረት ነው ስብሰባው የተካሄደው፡፡
በመጀመሪያው የአዲስ አበባ ምክክር ሶስቱ ሀገራት በግድቡ ውሃ አያያዝና አለቃቀቅ ዙሪያ አቋማቸውን አንፀባርቀው በስፋት መወያየታቸው ይታወሳል።
የካይሮው ውይይት በግድቡ የውሀ ሙሌትና አለቃቀቅ ዙሪያ ከሚደረጉ አራት ውይይቶች አንዱ ሲሆን ሶስተኛው ዙር ውይይት ከቀናት በኋላ በሱዳን ካርቱም ተካሂዶ አራተኛውና የማሳረጊያው ውይይት ደግሞ በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ የሚደረግ ይሆናል፡፡
ምንጭ፡-ኢቢሲ